Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ 17 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታዎች በካዳስተር ተመዘገቡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሶስት ወራት 17 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታዎች ላይ የካዳስተር ምዝገባ ተከናውኗል አለ የከተማዋ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ፡፡

ኤጀንሲው ለፋና ዲጂታል እንደገለጸው ÷ ከመሬት ይዞታ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው፡፡

የይዞታ ማረጋገጥ፣ የተረጋገጠና አዲስ ይዞታ ምዝገባ፣ የሥመ ንብረት ዝውውር እና የቋሚ ንብረት ምዝገባን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡

በተለይም የመሬት መረጃዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ አደራጅቶ ለመያዝ የሚያስችል የመሬት መረጃ አያያዝ ሥርዓት (ካዳስተር) ለማስፋፋት ትኩረት መደረጉ ተገልጿል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ሶስት ወራት በ17 ሺህ 385 የመሬት ይዞታዎች ላይ የካዳስተር ምዝገባ መከናወኑ ተጠቅሷል፡፡

በዚህም 39 ሺህ 48 ተገልጋዮች በማስተናገድ 3 ነጥብ 09 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘት የተቻለ ሲሆን ÷ ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት የመስጠቱ ሒደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል ፡፡

ዘመናዊና ሁለገብ የካዳስተር ግንባታ ሥርዓት በመዲናዋ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ኤጀንሲው አመልክቷል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.