Fana: At a Speed of Life!

ሰሜን ኮሪያ ባላስቲክ ሚሳኤል አስወነጨፈች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያ አቻቸው ኪም ጆንግ ኡን ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ካስታወቁ ከሰዓታት በኋላ ሀገሪቱ ባላስቲክ ሚሳኤል አስወንጭፋለች፡፡

ሰሜን ኮሪያ ባላስቲክ ሚሳኤሉን የተኮሰችው ወደ ምስራቅ የባህር ዳርቻ መሆኑን ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን አስታውቀዋል፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ካስታወቁ ከሰዓታት በኋላ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

ምንነቱ ያልተገለጸው ሚሳኤል የተተኮሰው ሰሜን ኮሪያ ከቻይና ጋር ድንበር ከምትዋሰንበት ሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል መሆኑን ነው የደቡብ ኮሪያ ጦር ያስታወቀው፡፡

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናይ ታካኢቺ በበኩላቸው ባላስቲክ ሚሳኤሉ ከጃፓን የኢኮኖሚ ዞን ውጪ መውደቁን ገልጸው፥ የደረሰው የጉዳት መጠን አለመታወቁን ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በደቡብ ኮሪያ ጉብኝት ያደረጉት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን ጋር ለመገናኘት ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸውን ይታወሳል፡፡

ኪም ጆንግ ኡን ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ለቀረበው የውይይት ሀሳብ የሰጡት ምላሽ ባይኖርም፥ ዋሽንግተን የሰሜን ኮሪያን የኒውክለር መሳሪያ ልማት መቃወሟን ካቆመች ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆቹ 2019 በመጀመሪያው ዙር የስልጣን ዘመናቸው ከኪም ጋር መገናኘታቸውን አስታውሶ የዘገበው ዘ ቴሌግራፍ ነው፡፡

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.