Fana: At a Speed of Life!

የመገጭ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክትን ከሰኔ በፊት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመገጭ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክትን ከሰኔ 2018 ዓ.ም በፊት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው አሉ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)።

የፕሮጀክቱ የስራ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የመገጭ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ በፍጥነት እና በጥራት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ህዝቡ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያነሳበት እንደነበር አስታውሰው፤ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት መንግሥት በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አመራር ሥራው ለአዲስ ኮንትራክተር መሰጠቱን እና ችግሩ ምን እንደሆነ በባለሙያ ተለይቶ በፍጥነት እንዲሰራ መደረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የውጭ አማካሪዎችን በማካተት፣ የፕሮጀክቱ ውስጣዊ ችግሮችን በመለየት እና ጥናት በማድረግ በግንባታ ሂደቱ ላይ ያጋጠሙ የቴክኒክ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት በፍጥነት እና በጥራት እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት አብርሃም በላይ (ዶ/ር)÷ የዋናው ግድብ የአፈር ሙሌት ስራ በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህ ሂደት በመቀጠል ከሰኔ 2018 ዓ.ም በፊት ዋናውን ግድብ ሙሉ ለሙሉ እንጨርሳለን ነው ያሉት።

የመገጭ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የወንዝ ቅልበሳ ሥራ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባወጡት መረጃ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ፕሮጀክቱ 870 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ÷ ሥራው ሲጠናቀቅ 17 ሺህ ሔክታር በመስኖ አቅርቦት ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.