ኢትዮጵያና ሳዑዲ በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ስምምነት ፈርመዋል።
በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) ከሳዑዲ ዓረቢያ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተቋማት ባለስልጣን (ሙንሻአት) ዋና ገዥ የሆኑት ሳሚ ኢብራሂም አልሁሰይኒ ጋር በሪያድ እየተካሄደ ካለው የቢባን 2025 ፎረም ጎን ለጎን ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማኅበር እና ሙንሻአት በዲጂታል እና ኢ-አገልግሎቶች ዘርፍ ትብብርን ለማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ትብብር ፈጥረዋል፡፡
በወቅቱም የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሳሚያ አብዱልቃድር እና የሙንሻአት የአጋርነት ዋና ስራ አስኪያጅ አብዱልሞህሰን ሳሌም የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነቱን ፈርመዋል።
አጋርነቱ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ እና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል በሚገኙ ሥራ ፈጣሪዎች እና ስታርት አፖች መካከል ያለውን ትብብር ያሳድጋል።
ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንባታን እና የገበያ ተደራሽነትን ለማገዝ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል።
እንዲሁም ዘላቂ የሥራ ፈጠራ ሥርዓቶችን ለማጠናከር የሚያስችል ትብብር መሆኑን በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመልክቷል።
በሚኪያስ አየለ