የጎንደር ከተማ በታደሰው የፋሲል ቤተመንግስት እና በሚሰሩት ፕሮጀክቶች ተሞሽራለች – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎንደር ከተማ በታደሰው የፋሲል ቤተመንግሥት እና በሚሰሩት ፕሮጀክቶች ተሞሽራለች አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የጎንደር ቤተ መንግሥት በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የተገነባ መሆኑን አስታውሰው÷ የታሪክ እና ማንነት መገለጫ እንደሆነም ተናግረዋል።
የቱሪዝም መዳረሻ የሆነው የጎንደር ቤተ መንግሥት መታደሱ ከክልሉ አልፎ ለሀገሪቱም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የመገጭ ግድብም ከዚህ ቀደም ተጓትቶ እንደነበር አንስተው÷ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በመንግሥት ቁርጠኛ ውሳኔ ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንደ አዲስ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ግድቡ ለጎንደር ከተማ የንጹህ ውሃ አቅርቦትን የሚያሻሽል፣ ኢኮ ሲስተሙን በተሻለ መንገድ የሚቀይር እና በመስኖ ልማት ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በጥራት እና በፍጥነት እየተሰራ የሚገኘው የአዘዞ መንገድ ሲጠናቀቅ የማህበረሰቡን የመንገድ ችግር የሚፈታ መሆኑን አንስተዋል።
ጎንደር በእነዚህ ፕሮጀክቶች ተሞሽራለች ያሉት አቶ አረጋ÷ የተሰሩ ስራዎች ጎንደርን ከበፊቱ የበለጠ የቱሪስት መዳረሻ እና ኢኮኖሚዋን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
የሚሰሩ የልማት ስራዎች በጎንደር ብቻ የሚያበቁ እንዳልሆኑና እንደ ክልል በደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ባሕር ዳር እና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ልማቶች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በሶስና አለማየሁ