በአማራ ክልል ከመስኖ ልማት 52 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ከመስኖ ልማት ከ52 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
ቢሮው ከመስኖ ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር በኮምቦልቻ ከተማ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው በመድረኩ እንዳሉት÷ ባለፉት አመታት ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በተሰጠው ትኩረት ስንዴ የማያመርቱ አካባቢዎች ጭምር ወደ ልማት እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል።
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ብቻ ከ10 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ በየደረጃው የንቅናቄ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሩ ያለውን የውሃ አማራጭ መጠቀም እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል በማለት ገልጸው፤ አርሶ አደሩ ቢያንስ አንድ የውሀ አማራጭ እንዲኖረው የከርሰ ምድር ውሀን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።
በዚህ ዓመት ከ331 ሄክታር ሺህ በላይ ነባር እና ከ51 ሺህ ሄክታር በላይ አዲስ በጥቅሉ ከ382 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከ52 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
ለመስኖ ልማቱ በቂ ግብዓት መቅረቡን በመጥቀስ፣ የማዳበሪያ እና የውሃ ፓምፖችን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በይከበር አለሙ