በመደመር መንግሥት ዕይታ እመርታዊ ለውጥ መጥቷል – ከፍተኛ አመራሮች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመደመር መንግሥት ዕይታ በዘርፎች ላይ የመጣውን እመርታዊ ለውጥ በተጨባጭ ማየት ችለናል አሉ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት በሀገሪቷ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ላይ ያጠነጠኑ ስልጠናዎችን ወስደዋል።
ስልጠናውን አስመልክተው ገለፃ ያደረጉት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፋ መሐመድ፤ ብልጽግና ፓርቲ ብዝሃ ዘርፍ ላይ ትኩረት በማድረግ በርካታ ድሎችን አሳክቷል ብለዋል።
በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ በከተሞች ልማትና በቱሪዝም ዘርፎች የተደረጉ ሪፎርሞችና የተገኙ ውጤቶች ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር መሰረት መጣላቸውንም አንስተዋል።
በፓርቲው የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና በመደመር እይታ በፈጠራና በፍጥነት ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሰተዳደር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ ስልጠናው ኢትዮጵያ ያላት ጸጋዎች ከራሷ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ መሆኑን ያየንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከቀጣናው አልፋ ከዓለም ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ የመሆን አቅም እንዳላትና ለዚህ ደግሞ አመራሩ በቁርጠኝነት እንዲሰራ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ስልጠናው በመደመር መንግሥት ዕይታ በዘርፎች ላይ የመጣውን እመርታዊ ለውጥ በተጨባጭ ማየት ያስቻለ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።