Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን የውጭ ምንዛሪን እያስቀረ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በተጠናከረ ሁኔታ በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪን እያዳነ ነው አሉ የግሩፑ ም/ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል ኦላኒ፡፡

አቶ ዳንኤል ኦላኒ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረቱ ሥራ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡

ግሩፑ የተለያዩ ትራክተሮችን፣ የማሽንና የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎችን፣ የግንባታ ማሽነሪዎችን፣ ትራንስፎርመር፣ ለኮሪደር ልማት የመንገድ ላይ ፖል እና ሌሎች ምርቶችን በጥራት እያመረተ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም የግብርና ልማትን የሚያሳድጉ የእርሻ መሳሪያዎችን በመገጣጠምና በማምረት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የትራክተር ተቀጽላዎችን ማለትም ማረሻ፣ መከስከሻ፣ መውቂያ እንዲሁም የመስኖ የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን በስፋት በማምረት እንደሚያሰራጭም አመልክተዋል፡፡

በዚህም በርካታ የውጭ ምንዛሪን ከማዳን ባለፈ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡

ቴክኖሎጂ በማፍለቅ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል፡፡

ግሩፑ በቀጣይ ተኪ ምርቶችን ለማምረት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን ከፍተኛ ተልዕኮ ይዞ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ሥር የተለያዩ ስትራቴጅክ ምርቶችን የሚያመርቱ 7 ኩባንያዎች መኖራቸውን አቶ ዳንኤል ኦላኒ ተናግረዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.