ኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ውጤታማ ተሞክሮዋን በቀጣናው ለማስፋት ቁርጠኛ ናት – ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችውን ስኬት በምስራቅ አፍሪካ ለማስፋት ተሞክሮዎቿን ለማጋራት ቁርጠኛ ናት አለ የግብርና ሚኒስቴር።
19ኛው የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ቀጣናዊ የባለድርሻ አካላት መድረክ “ለተፋጠነ የግብርና ምርት ሰንሰለት ስርዓት ሽግግርና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ትብብርና ኢንቨስትመንትን ማጠናከር” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት የፖሊሲዎች፣ ጥናትና ምርምሮች እንዲሁም የአርሶ አደሮች ተሳትፎ መጣጣም ውጤት ማምጣት እንደሚችል ማሳያ ነው።
አካባቢን መሰረት ያደረገና ገበያ ተኮር ምርትን ማስፋፋት፣ ድህረ ምርት የሚደርሰውን ኪሳራ መቀነስ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግን ማስፋፋትና የገጠር ስራ ፈጠራ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም መንግስት አዳዲስ ፈጠራዎችን ከምርምር ማዕከላት ወደ ማሣ ለማሸጋገር በምርምር፣ በግብርና ኤክስቴንሽንና በአርሶ አደሮች ስልጠና ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ልማት በትኩረት እየሰራች መሆኑን አንስተው፥ ዘርፉ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በቀጣናው የተቀናጀ ኢንቨስትመንት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ስትራቴጂዎች ከፋኦ ቀጣናዊ የግብርና ምርት ሰንሰለት ስርዓት ለውጥ ማዕቀፍ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ጠቅሰው፥ እነዚህን አቀናጅቶ መስራት የምግብ አቅርቦትን ለማሳደግ፣ ስርዓተ ምግብን ለማሻሻልና የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በግብርና መስክ እያስመዘገበችውን ያለውን ስኬት በተለይም በስንዴ ልማት የመጣውን ውጤት ተሞክሮዋን ለቀጣናው ሀገራት ለማጋራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በኃይለማርያም ተገኝ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!