ኦቪድ ሪል ስቴት ለ15 ቀናት የሚቆይ ታላቅ የሽያጭ ኤክስፖ አዘጋጀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኦቪድ ሪል ስቴት ከሕዳር 22 እስከ ታህሳስ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ለ15 ቀናት የሚቆይ ታላቅ የሽያጭ ኤክስፖ አዘጋጅቷል።
የድርጀቱ የማርኬቲንግ ማናጀር መቅደስ ቀደመ እንዳሉት÷ ድርጅቱ በርካታ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ይታወቃል።
ሁሉም ሰው እንደ አቅሙ ሊገዛቸው የሚችሉ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በከፍተኛ ጥራት እየገነባ ይገኛል በማለት ገልጸው፤ በተከታታይ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ደንበኞቹን ሲያስተናግድ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከሕዳር 22 እስከ ታህሳስ 6 ቀን 2018 ዓ.ም በሚቆየው የሽያጭ ኤክስፖ በገርጂ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ በአራት ኪሎ ጥይት ቤት፣ በጎልፍ ክለብ፣ በኢትዮ ኩባ እና ገላን ጉራ አምስት የግንባታ ሳይቶች የሚገኙ ቤቶችን በቅናሽ ዋጋ ለሽያጭ አቅርቧል።
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ለሚገዙ ደንበኞች አድርጎት የነበረውን የዋጋ ቅናሽ በማጠናቀቅ ከታህሳስ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የዋጋ ማስተካከያ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
በዚሁ መሰረት በኤክስፖዉ ቤት ለመግዛት የሚፈልግ ሁሉ የዋጋ ቅናሹ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል።
ቤቶቹ ግንባታቸው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ የቤት ዕቃ የተሟላላቸው እና በከፊል ግንባታዎች የተጠናቀቁ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
አቪድ ሪል ስቴት አሁን ላይ በ570 ሄክታር መሬት ላይ 60 ሺህ ቤቶችን በመገንባት ከተማን እየመሰረተ የሚገኝበት ኦቪድ ገላን ጉራ ፕሮጀክትን ጨምሮ በሰባት የተለያዩ ቦታዎች ፕሮጀክቶችን በፍጥነት እየሰራ እንደሚገኝ ወ/ሮ መቅደስ ተናግረዋል።
በዙፋን አምባቸው