Fana: At a Speed of Life!

ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮችን ሲፈጽሙ የተደረሰባቸው 112 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተቀናጀ መንገድ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮችን ሲፈጽሙ የተደረሰባቸው 112 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ዲጂታል እንደገለጸው ÷ መንግሥት ተግባራዊ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በመጻረር በተደራጀ መንገድ በሚፈጽሙ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮች ዙሪያ በተቀናጀ መልኩ ምስጢራዊ የመረጃ ስምሪት ሲከናወን ቆይቷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የክልል የፀጥታ አካላትና በሕብረተሰቡ ጥቆማ በተደረገ የተቀናጀ ሥምሪት በፋይናንስ አሻጥር የተሰማሩ 112 ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

ከሕገ ወጥ ተግባሩ ጋር ትስስር የነበራቸው 519 የባንክ አካውንቶች የታገዱ ሲሆን ÷ የተለያዩ ኤግዚቢቶች መያዛቸውም ተጠቅሷል፡፡

ሕገ ወጥ ሃዋላዎች ፣ የገንዘብ ዝውውሮች፣ የውጭ ምንዛሪ ስወራዎች ፣ የግብር ስወራዎች፣ ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ የማስመሰልና ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትሉ እንዲሁም አሸባሪዎችንና የታጠቁ ቡድኖችን ለመደገፍ ሲውሉ መቆየታቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡

በተለይም ሕገ ወጥ በሆኑ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች፣ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎች፣ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያዎች፣ ሕገ ወጥ የሃዋላ አዘዋዋሪዎችና ደላላዎች፣ በወጪና ገቢ ንግድ ላይ አሻጥር የፈፀሙ አስመጪዎችና ላኪዎች እንዲሁም ሕጋዊ ንግድ ሳይኖራቸው በሕገ ወጥ ሃዋላ ላይ በመሰማራት ከፍተኛ ገንዘብ በማንቀሳቀስ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሱ አካላት የማያዳግም ሕጋዊ ርምጃ መወሰዱ ተጠቁሟል፡፡

በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚልኩት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ የብሔራዊ ባንክን መመሪያ በሚጥስ ሁኔታ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትሉ የቆዩ ሕጋዊ ፈቃዳቸው በፈጸሙት ተደጋጋሚ ጥፋት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰረዘባቸው ዓለም አቀፍ የሃዋላ አስተላላፊዎችና ሕገ ወጥ የሃዋላ ድርጅቶችም ርምጃው የተወሰደባቸው ናቸው።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ሀብትን ከሀገር በማሸሽ ላይ ያሉ ድርጅቶች ባለቤቶችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የብሔራዊ ባንክ ሕግን በሚጥስ ሁኔታና ያለምንም ፈቃድ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያን በመጠቀም በሕገ ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪን ሲያዘዋውሩ የነበሩ አካለት ላይም ርምጃ ተወስዷል፡፡

በሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ላይ በማነጣጠር ሲፈጸም የነበረው ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ለማስተጓጎል፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዲያድርበት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዳያንሰራራ በተቀናጀ መንገድ ሲፈጽሙት እንደነበረ ነው የተገለጸው፡፡

የሀገርን ደኅንነት ስጋት ላይ በሚጥሉ እና የሀገርን ኢኮኖሚ በሚጎዱ አሻጥሮች ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በመከታተል የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡

መላው ሀገር ወዳድ ዜጋ መሰል ወንጀሎችንና ወንጀለኞችን በማጋለጥ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.