በአርሲ ዞን የተከሰተውን ችግር እንዲያጣራ የተሰየመው አጣሪ ኮሚቴ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የተከሰተውን ችግር እንዲያጣራ የተሰየመው አጣሪ ኮሚቴ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በአርሲ ዞን በጉና፣ መርቲ፣ ሸርካ እና ሆሎንቆ ዋቢ ወረዳዎች የተፈጠረውን ችግር እንዲያጣራ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ተወካዮችን ያካተተ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ችግር ወደ ተከሰተባቸው ወረዳዎች ማሰማራቱ ተመላክቷል፡፡
ኮሚቴው በአራት የአርሲ ዞን ወረዳዎች በአካል በመሄድ ጉዳዩን ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲያጣራ ቆይቶ በአጣሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ እና ም/ሰብሳቢ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ መሰረትም በወረዳዎቹ የሰዎች መገደል፣ መታጋት እና የንብረት ውድመት መከሰቱን ከአካባቢው ማሕበረሰብና ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖች መረጃ ማግኘቱን አጣሪ ኮሚቴው ገልጿል፡፡
የተገደሉት ሰዎች እንዲሁም የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ያጋጠማቸው ዜጎች የአንድ የሃይማኖት ተከታይ እና አገልጋዮች አለመሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በአካባቢው ሃይማኖት እና ዘር ሳይለይ ግድያ እና ጥቃት መፈጸሙ ነው የተመላከተው፡፡
ይህን ወንጀል የፈጸሙት አካላትም ራሳቸውን በተለያየ ስም የሚጠሩና የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ችግር ወደ ተከሰተባቸው ስፍራዎች ሲንቀሳቀስ ስፍራዎቹን በፍጥነት በመልቀቅ በጫካ የሚደበቁ የታጠቁ ኃይሎች መሆናቸውን ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው የአካባቢው ማሕበረሰቦች ኮሚቴው መረዳት ችሏል፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ መላዕከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ችግሩ ተጋላጭ የአንድ ወገን ብቻ ያነጣጠረ አለመሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ሐጅ አብዱልሃኪም ሁሴን በበኩላቸው ÷ ችግሩ ብሔር ወይም ሃይማኖት መሰረት ያደረገ አለመሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
አጣሪ ኮሚቴው በአካባቢው ለሚገኙ ዜጎች በቂ ጥበቃ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ማመልከቱንም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡