የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‘ሲቢኢ በእጄ’ የተሰኘ የዲጂታል ቁጠባና ብድር አገልግሎት አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‘ሲቢኢ በእጄ’ የተሰኘ የዲጂታል ቁጠባ እና ብድር አገልግሎት በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ተወካይ እና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪውቲቨ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አፍሬም መኩሪያ እና የሌሎች ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
አቶ ኤፍሬም በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ንግድ ባንክ ዘመኑን የዋጁ አዳዲስ አገልግሎቶችን በማፍለቅ ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት እየሰጠ ነው።
የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ዲጂታል ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
‘ሲቢኢ በእጄ’ ዲጂታል የቁጠባና ብድር አገልግሎት እስከ 150 ሺህ ብር ድረስ ብድር ያለማስያዣ ማግኘት ያስችላል ብለዋል።
አገልግሎቱን ለማግኘትም ተቋማት የሠራተኞችን ወርሃዊ ደመወዝ በሲቢኢ ብር ለመክፈል ስምምነት መፈጸም እንዳለባቸው አብራርተዋል።
በአገልግሎቱ የመንግስት ሰራተኞችን ቅድሚያ ተጠቃሚ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች ተደርገዋል ነው ያሉት።
ባንኩ እስከአሁን ከ478 ኩባንያዎች ጋር ተፈራርሞ ስምምነቱ ከጸደቀላቸው 83 ድርጅቶች ለተወጣጡ ሠራተኞች በ’ሲቢኢ በእጄ’ ዲጂታል ባንክ ብድር መስጠቱን አንስተዋል።
በዚህም ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ብድር መስጠቱን አብራርተዋል።
በመላኩ ገድፍ