የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአማራ ክልል ያሳየው ለውጥ የኢንዱስትሪ አብዮት ሊባል የሚችል ነው – አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና ደብረ ብርሃን ከተማ ያሳየው ለውጥ የኢንዱስትሪ አብዮት ሊባል የሚችል ነው አሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል።
ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በደብረ ብርሃን ከተማ ተገንብቶ የተጠናቀቀውን የብራውን ፉድስ የበቆሎ ማቀነባበሪያ እና የምግብና የእንስሳት መኖ ማምረቻ ፋብሪካ ምረቃ ወቅት ነው።
ከለውጡ በፊት በሰሜን ሸዋና ደብረ ብርሃን ከተማ 18 አምራቾች ብቻ እንደነበሩ አስታውሰው÷ በአሁኑ ሰዓት በደብረ ብርሃን ከተማ ብቻ 105 እንዲሁም በሰሜን ሸዋ 87 መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ይህም በአማካኝ በየዓመቱ 24 መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውን እንደሚያሳይ አንስተው÷ መንግስት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሰፋፊ ስራዎች መስራት ችሏል ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል በቆሎ በግብዓትነት ይጠቀማልም ነው ያሉት።
የፋብሪካው ምርት ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚመጡ ሰብአዊ ችግሮች እንደሚፈታና የሚመረተው የእንስሳት መኖም ለእንስሳት ሃብት ልማት እድገት አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
በለይኩን ዓለም