የዓለም መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ኮፕ32ን እንድትዘጋጅ ስለመመረጧ ምን አሉ?
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤን (ኮፕ32) በፈረንጆቹ 2027 እንድታስተናግድ መመረጧ በብራዚል ቤለም በተካሄደው ኮፕ30 ላይ ይፋ ሆኗል።
ኢትዮጵያ መመረጧን ተከትሎ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን ሰፊ ሽፋን እየሰጡት ይገኛል፡፡
የኮፕ30 ጉባኤ ፕሬዚዳንት አንድሬ ኮሪያ ዶ ላጎ እና በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑል ሰገድ ታደሰ የጉባኤው ተሳታፊ ሀገራት ኢትዮጵያ ሁነቱን እንድታስተናግድ መስማማታቸውን ገልጸዋል።
አፍሪካ ኒውስ ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው ሀተታ÷ ኢትዮጵያ ባለፈው መስከረም ወር የተካሄደውን 2ኛውን የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤን በተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷን አስታውሷል።
ኢትዮጵያ የምታስተናገደው ኮፕ32 በአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ተጎጂ ለሆነችው አፍሪካ መፍትሄ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት የማገዝ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አብራርቷል፡፡
ኢንዲያን ኤክስፕረስ ባወጣው ዘገባ÷ የአፍሪካ ሀገራት ከበለፀጉ ሀገራት በተቃራኒ ለካርበን ልቀት ዝቅተኛ አስተዋፅኦ ቢኖራቸው የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸው ጉዳቶችን እንደሚያስተናግዱ አንስቷል፡፡
ኮፕ32 ሁሉን አቀፍ እና ፍትሃዊ የአየር ንብረት ለውጥ ሽግግር እንዲኖር እንዲሁም የካርበን ልቀትን ለመቀነስ እና የአየር ንብረትን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋኦ ያደርጋል ብሏል፡፡
በተመሳሳይ ሲኤንቢሲ አፍሪካ ኢትዮጵያ የያዘቻቸው የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲዎች ናይጀሪያን በመብለጥ የኮፕ32 አዘጋጅ ሆና እንድትመረጥ አስችሏታል ብሏል፡፡
ኤፒኤ ኒውስ፣ ክላይሜት ሆም ኒውስ፣ አርቲኢ፣ ፍራንስ 24 እና ዘ ኒው አረብ ኢትዮጵያ ኮፕ32ን እንድታስተናግድ መመረጧን በተመለከተ ሰፊ ሽፋን ሰጥተዋል።
በሚኪያስ አየለ