የአንተነህ ጸጋዬ (ዶ/ር) ቀብር ሥነ ሥርዓት የፊታችን ቅዳሜ ይፈጸማል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና የሥነ ተግባቦት መምህር የነበሩት አንተነህ ጸጋዬ (ዶ/ር) ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
በዩኒቨርሲቲው ለረጅም ዓመታት በማስተማርና ምርምር ሥራዎች ያገለገሉት አንተነህ ጸጋዬ (ዶ/ር) ባጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ነው በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፡፡
የአንተነህ ጸጋዬ (ዶ/ር) አስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር ነገ 5 ሰዓት ላይ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸውም ሕዳር 6 ቀን 2018 ዓ.ም 6 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ቦሩ አካባቢ በሚገኘው የፕሮቴስታንት መካነ መቃብር እንደሚፈጸም ቤተሰቦቻቸው ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
አንተነህ ጸጋዬ (ዶ/ር) ጀርመንን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ሀገራት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
ሕይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስም በመገናኛ ብዙሃን በመቅረብ በብሔራዊ አጀንዳና ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ትንታኔዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡
አንተነህ ጸጋዬ (ዶ/ር) ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአንተነህ ጸጋዬ (ዶ/ር) ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል።