ምቹ የፋይናንስ ሥርዓት ለስታርት አፕ ቢዝነሶች…
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት ለስራ ፈጣሪዎችና ስታርት አፕ ቢዝነሶች ምቹ የፋይናንስ ስርዓት ዘርግቷል አሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል።
ሚኒስቴሩ በሥራ ዕድል ፈጠራ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አዳዲስ የፈጠራ ሐሳብ የሚያመነጩ ስራ ፈጣሪዎችና ስታርት አፕ ቢዝነሶችን መደገፍና ለውጤታማነት ማብቃት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዘርፉ ተዋንያን የራሳቸውን ሚና መጫወት እንዲችሉና የፋይናንስ ስርዓቱ ለስራቸው ምቹ እንዲሆን የኢንቨስትመንት ልማት ባንክን ጨምሮ ዘርፉን የሚያጠናክር ስርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
ይህም የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ አቅርቦት ተግዳሮቶችና ስጋቶችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል አስረድተዋል።
ወጣቶች ክህሎታቸውንና የፈጠራ ስራዎቻቸውን የሚያጎለብት፣ ሐሳቦቻቸውንም እስከ ትላልቅ ፋብሪካዎች ማድረስ የሚያስችል ድጋፍ እየተሰጣቸው መሆኑን አንስተዋል።
ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት አንዲያሸጋግሩ የሚያስችል ምቹ ምህዳር እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው÷ መንግሥትም ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ስታርት አፕ ቢዝነሶች ወሳኝ ሚና በመጫወት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ሚኒስትሯ አመላክተዋል።
በሶስና አለማየሁ