Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በሌማት ትሩፋት የእንቁላል ምርታማነትን ለማሳደግ…

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የእንቁላል ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡

የቢሮው ም/ሃላፊና የእንስሳት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ቶሌራ ደበላ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በክልሉ በእንስሳት ዘርፍ ልማት እየተተገበረ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡

በፕሮግራሙ የወተት፣ ማር፣ እንቁላል እና አሳ ምርታማነትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ የዶሮ ስጋ እና የእንቁላል ምርትን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አመልክተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የዶሮ ዝርያዎችን በማሰራጨት የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በተከናወነው ሥራ ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

በዶሮ እርባታ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት መጠናከሩን ጠቁመው ÷ በበጀት ዓመቱ 100 ሚሊየን የተሻሻሉ የዶሮ ጫጩቶች ለማሰራጨት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሩብ ዓመቱም 26 ሚሊየን በላይ የተሻሻሉ እና ምርታማነታቸው የተረጋገጠ የዶሮ ጫጩቶች መሰራጨታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በ2018 ዓ.ም 6 ነጥብ 5 ቢሊየን እንቁላል ለማምረት ታቅዶ ባለፉት 3 ወራት 432 ሚሊየን እንቁላል ማምረት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል 35 ሺህ ቶን የዶሮ ስጋ መመረቱን ጠቁመው ÷ በቀጣይ በመርሐ ግብሩ የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ከገበያ ትስስርና ከመኖ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በተዋረድ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት የእንስሳት ተዋጽኦ ምርትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት አጋዥ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.