Fana: At a Speed of Life!

ብርሃን ተለግሳ ለማመስገን የቆመች ነፍስ…

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቤዛዊት ጥላሁን ሁለቱንም የዓይን ብርሃኗን ያጣችው ድንገት ነበር። የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለች በ12 ዓመቷ።

ድንገት በተከሰተው ዓይነ ስውርነት እሷም ሆነች ቤተሰቧ መደናገጣቸው አልቀረም። እንደ እኩዮቿ ትቦርቅ የነበረችው ቤዛ ቁዘማ ውስጥ ገባች፡፡

እንደፈለጉ ይወጡ ይገቡ የነበሩት እግሮቿ ምድርን መርገጥ ፈሩ፤ ይርዱ ይርበተበቱ ጀመር፤ ያለ ሰው ድጋፍ ምንም ማድረግ ተሰናት።

እንዴት ለምን የሚሉ መልስ ያጣችባቸው ጥያቄዎች ደግሞ ወደ አዕምሮዋ እየተመላለሱ ሰላም ነሷት። በእንቅርት ላይ… እንዲሉ ሁኔታውን መቀበል አቅቷት ወደ አዕምሮ ሐኪም ለመሄድ ተገደደች።

ቤዛዊት “እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ ብዙ ችግሮችን አሳልፈናል” ትላለች በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ስታስታውስ ፡፡

ለአራት ዓመታት ያህል በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ካለፈች በኋላ ቤዛዊት የዓይን ብሌን ለጋሽ እንደተገኘላት ሰማች፤ በተሳካ ሁኔታም ሕክምናው ተከናወነ።

አሁን ቤዛዊት ሁለቱም ዓይኖቿ መመልከት ችለዋል። “ለጋሾቼን ሕልወታቸው አልፎ ባላውቃቸውም ለእኔ ብርሃን ሰጥተውኛልና ሁሌ ከእንቅልፌ ስነቃ ነፍሳቸውን ማርልኝ እያልኩ ፀሎት አደርሳለሁ” ትላለች

እንደ ቤዛዊት ሁሉ ሌሎች በበጎ አሳቢ ወገኖቻቸው ምክንያት የዓይን ብርሃናቸው ተመልሶላቸዋል።

ሆኖም ብርሃንን አጥቶ በተለይ ለጋሽ ከተገኘ መዳን እንደሚችል እያወቁ ዓመታትን በተስፋ መቆየት የብዙዎች እጣ ሆኗል።

በኢትዮጵያ መዳን በሚችለው በዓይን ብሌን ጠባሳ ሳቢያ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎች የዓይን ብርሃናቸውን ተነጥቀዋል።

ከሞቱ በኋላ የዓይን ብሌናቸው ለሌላ ሰው እንዲሰጥ የሚናዘዙ ሰዎች ቁጥር አናሳ መሆን ችግሩን እንዳባባሰው ይነገራል።

የደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አሸናፊ ታዘበው (ዶ/ር) ከግንዛቤ እጥረት አልያ እምነቴ አይፈቅድም በሚል ብዙዎች ይሄንን ለማድረግ አይደፍሩም ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ የእምነት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎች አባገዳዎችና ሀደሲንቄዎች ጋር በመስራት በጉዳዩ ላይ ለውጥ ለማምጣት እንቅስቃሴ መጀመሩን አንስተዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ሶስት ወራት 1 ሺህ 200 ያህል ሰዎች ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል እንደገቡ ተናግረዋል።

የዓይን ብሌን ልገሳ የንቅናቄ ወር በዓለም ለ42ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

የዓይን ብሌን የተለገሰላት ቤዛዊት መመልከት ከጀመረች በኋላ ከሰባተኛ ክፍል ያቋረጠችውን ትምህርት ቀጥላ በቴአትር ጥበባት ተመርቃለች፤ በትዳር ተባርካም የአንድ ልጅ እናት ሆናለች።

በሳራ መኮንን

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation

Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting

Facebook https://web.facebook.com/fanasport

Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate

Telegram t.me/fanatelevision

Website www.fanamc.com

TikTok www.tiktok.com/@fana_television

WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29

Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment

TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment

Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.