Fana: At a Speed of Life!

አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር እና የአፍሪካ ህብረት ተጠሪ አሌክሲስ ላሜክ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በፈረንጆቹ 1897 የጀመረው የኢትዮ-ፈረንሳይ ታሪካዊ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረሱ ተገልጿል።

ባለብዙ ወገን የሆነው የሀገራቱ ግንኙነት በጂኦስትራተጂክ ትብብር፣ በመሰረተ ልማት፣ በባህል ልውውጥ እንዲሁም በተቋማት ልማት እየተጠናከረ ስለመምጣቱ መክረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መካከል ባለው ጠንካራ ትብብር የሀገራቱ ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱም ተመላክቷል።

ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ፣ የቅርስ ጥበቃ፣ የመልካም አስተዳደር ኢኒሼቲቮች፣ የዴሞክራታይዜሽን ሂደት፣ የቴክኖሎጂ መሻሻል፣ የተቋማት ግንባታ እና ሀገራዊ አንድነት የማጠናከር ሂደትን እየደገፈች ትገኛለች።

አቶ አደም ፋራህ በወቅቱ ባደረጉት ገለጻ፤ በብልጽግና ፓርቲ አመራር በፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በፖለቲካው መስክ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች ሚኒስትርነትን ጨምሮ በመንግሥት የስራ ኃላፊነት ላይ ተመድበው እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የተቋማት ሪፎርም ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው፤ ለአብነትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቅሙን አጠናክሮ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በብቃት ለማከናወን በሚችልበት ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቅራኔዎችን ለመፍታት እና ዘላቂ ሀገራዊ አንድነትን እውን ለማድረግ የመጀመሪያውን ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ሀገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ ትርክት መገንባት የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት አስኳል ሆኖ እየተሰራበት እንደሆነም አስረድተዋል።

አምባሳደር ላሜክ በበኩላቸው በብልጽግና ፓርቲ አመራር ሰጪነት በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ላለው ለውጥ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፤ በተጨባጭ የሚታየውን የተቋማት ውጤታማነት፣ የመሰረተ ልማት ትስስር መስፋፋት እና የከተሞችን ፈጣን እድገት አድንቀዋል።

በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 18 ወራት ውስጥ ብቻ የታየው ለውጥ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ግዙፍ የሆነውን ሽግግር እያከናወነች ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ለዚህም የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ሪፎርም፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የዓለም አቀፍ መድረክ ንቁ ተሳትፎ ዋና ሞተር መሆኑን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.