Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጥቅምት እና ሕዳር ወር 2018 ዓ.ም ያከናወኑት ቁልፍ ተከታታይ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግባራት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጥቅምት እና ሕዳር ወር 2018 ዓ.ም ቁልፍ የሆኑ ተከታታይ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግባራትን አከናውነዋል።

በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ በመታደም ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት አስገኝተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ላይ መሳተፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የአፍሪካን የጋራ ድምጽ ለማጉላት ያስቻለ ነበር። ይህም የአህጉሪቱ ተጽዕኖ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እየጎለበተ መምጣቱን ያረጋግጣል።

የመስኖ ልማት ፕሮጀክት እና የቱሪዝም ልማት እንቅስቃሴን በተመለከተ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ በነበራቸው ጉብኝት የመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን የሥራ ሁኔታ ገምግመዋል። ፕሮጀክቱ 870 ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ 17000 ሄክታር መሬት በመስኖ አቅርቦት ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል። በጥቅሉ የመገጭ ግድብ በሚጠናቀቅበት ወቅት የአካባቢውን የግብርና ምርታማነት በመሠረቱ የሚያሳድግ ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚያው በጎንደር ከተማ ምልከታቸውን ሲቀጥሉ፥ ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የታደሰውን የፋሲል ጊቢ መርቀዋል። በግቢው የተከናወነው ሰፊ የእድሳት ሥራ በቅርስ ስፍራው ነባሩን ታሪክ በመጠበቅ ውበቱን እና ተደራሽነቱን በማሻሻል አዲስ እስትንፋስ የሰጠ ሆኗል። የእድሳት ሥራው የቤተመንግሥቱን የግንባታ መዋቅር መጠገን፣ የእግር መንገዶችን ማሻሻል፣ ቁልፍ የሆኑ ሕንፃዎችን ከዝግባ እና ዋንዛ በባሕላዊ ቁሳቁሶችን ተጠቅሞ በማደስ የስፍራውን ግለ ወጥ መልክ እና ባሕርይ ለመጠበቅ ተሰርቷል።

ለጎብኝዎች ምቾት የተሰናዱ አገልግሎት መስጫዎችም ትርጉም ባለው ደረጃ ተሻሽለዋል። አዲስ የቱሪስት ማዕከልም ተከፍቷል። ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች፣ የተሻሻሉ የመብራት እና የደኅንነት ሥርዓቶችም ተሰናድተዋል። እንደ አፄ ፋሲል፣ አፄ ቀዳማዊ ዮሃንስ እና አፄ ቀዳማዊ ኢያሱ አቢያተ መንግሥት ብሎም ድልድዮች፣ መታጠቢያ ሥፍራዎች፣ ታሪካዊ በሮች ወዘተ በጥንቃቄ ታድሰዋል። በተጨማሪም ከ40,000 ስኴር ሜትር በላይ የአካባቢው ምድር የማስዋብ ሥራ ተሰርቷል። ይኸም ለጎብኝዎች ይበልጥ ሳቢ የሆነ ከባቢ ፈጥሯል። አጠቃላይ የእድሳት ሥራው ከአንድ አመት በታች የፈጀ ሲሆን የዚህን አስደናቂ የታሪክ እና የባሕል ሥፍራ ለረዥም ጊዜ ጠብቆ በሚያቆይ አኳኋን ተከናውኗል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጎርጎራ ጣናነሽ ፪ የተሰኘችዉን ጀልባ ሥራ አስጀምረዋል። ከ180 ተጓዦች በላይ የማጓጓዝ አቅም ያላት ጣናነሽ ለጉብኝት፣ ለመዝናናት እና አስደማሚውን የጣና ሀይቅ የተፈጥሮ ከባቢ ለመጎብኘት ወደ ጎርጎራ ኤኮ ሎጅ የሚደረገውን ጉዞ የበለጠ ምቹ እያደረገችው ትገኛለች።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በባህር ዳር ከተማ በነበራቸው ጉብኝት፥ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን እንዲሁም ከተማዋን ለቱሪዝም ዘርፍ ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ተመልክተዋል። የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) ባስቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት ደረጃውን የማሻሻል ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ እንደሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተመልክተዋል። ስታዲየሙ 52 ሺህ ተመልካቾችን መያዝ የሚችል ሲሆን የወንበር መግጠምና የሳር ንጣፍ ስራዎች ተጠናቀዋል። የመብራት ዝርጋታን ጨምሮ ሌሎች የስታዲየም ውስጥ መሰረተ ልማቶችም በፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን መሠረት በማድረግ በባህር ዳር ጣና ሀይቅ ዳርቻ እየተገነባ ያለው ፈለገ ጊዮን ሪዞርትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የተመለከቱ ሲሆን፤ ሪዞርቱ ወደ ስራ ሲገባ የከተማዋን ቱሪዝም ከማነቃቃት ባሻገር ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር ይሆናል ሲሉ በወቅቱ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በዚሁ ወር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአማራ ክልላዊ መንግሥት ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር መቀመጫ የሆነችውን ከሚሴ ከተማን የጎበኙ ሲሆን፥ በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ በጅምር ደረጃ ያለ ቢሆንም የ1.3 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ እና የእግረኛ መንገድ ሥራዎች የሚመሰገኑ ናቸው ብለዋል። የኮሪደር ልማት ሥራ የሕዝባዊ ሥፍራዎችን ደረጃ ከፍ በማድረግ ዕሳቤ በሁሉም ደረጃ በመላው ኢትዮጵያ እየተተገበረ መሆኑን እንደሚያሳይም ገልጸዋል። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒትሩ በከተማዋ ለሌማት ትሩፋት ሥራ አስተዋጽዖ እያበረከተ ያለውን የኤልፎራ አግሮ-ኢንዱስትሪ የተቀናጀ የግብርና ልማት ፋብሪካንም ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ እምርታ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ዋና መስሪያ ቤቱን ቀድሞ ከነበረበት መለወጡን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በስፍራው ተገኝተው እንቅስቃሴውን ተመልክተዋል። በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ አስደናቂ የግንባታ ለውጥ እና ዘመናዊ የመሥሪያ ሥፍራ ጥበብን በማሳየት ለሠራተኞቹ እጅግ ምቹ የሆነ ስፍራንም መፍጠር እንደቻለም በጉብኝታቸው ወቀት ገልጸዋል። ተቋሙ በአምስት አመታት ጊዜ በጤና፣ በግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፍ እያደረገ ያለው የመሪነት አስተዋፅኦውን እየተወጣ ሲሆን፥ በክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ ትላልቅ የመረጃ ቋቶች፣ የመረጃ ፍለጋ፣ ሮቦቲክስ እና ኢመርሲቭ ቴክኖሎጂዎች አቅሙን በማጎልበት ላይ ይገኛል ብለዋል። በቅርቡ የተጀመረው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስታርት አፕ መዐከል ዜጎች ሀሳብ ብቻ ይዘው በመምጣት ፕሮቶታይፕ ለመፍጠር፣ ለማባዛት ብሎም ከግሉ ዘርፍ ኢንቬስተሮች ጋር እንዲገናኙ እድል ያመቻቻል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እስከ አሁን 200 ሀሳብ ፈጣሪዎች በዚህ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በዚሁም ወር ነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 50ኛ መደበኛ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ የወሰነው፡፡

በቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ ጥቅም የሚያጸኑ የሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ደፕሎመሲያዊ ተግባራትን አሳክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ዋዜማ የአስተናጋጇ ሀገር ፕሬዝደንት ከሆኑት ሲሪል ራማፎሳ ጋር ተገናኝተዋል። በተመሳሳይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጉባኤ ጎን ለጎን ከIMF ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂኦርጂየቫ ጋር በአለም አቀፍ የኢኮኖሚ አዝማሚያዎች፣ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም እንዲሁም ዘላቂ እና አካታች እድገትን ለመደገፍ ትብብርን ለማጠናከር ስላሉ እድሎች ላይ ተወያይተዋል። እንዲሁም ከአዲሱ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት ዶክተር ሲዲ ኡልድ ታህ ጋር ተገናኝተው፥ ባንኩ በመላው አፍሪካ አካታች እድገት እንዲኖር የሚያደርገውን ወሳኝ ሚና በሚያጠናክርበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን በርከት ያሉ ሀገራት መሪዎችን አግኝተው በሁለትዮሽ እና ስትራቴጂካዊ ትብብር ላይ የተወያዩ ሲሆን፥ የአቡዳቢው ልዑል አልጋ ወራሽ፣ የቱርክዬው ፕሬዝደንት፣ የፊንላንዱ ፕሬዝደንት፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት እና የጀርመኑ ቻንሰለር የሚጠቀሱ ናቸው። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም ከህንድ፣ ቬይትናም፣ ደቡብ ኮሪያ እና አውስትራሊያ መሪዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል። እንዲሁም ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከብራዚል ፕሬዚዳንት፣ ከኔዘርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከኢንዶኔዥያ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር መልካም ውይይት አድርገዋል። ውይይታቸውም የአየር ንብረት ጥበቃ ሥራ ትብብርን፣ ቅድሚያ በሚሰጣቸው በንግድ እና በምግብ ሉዓላዊነት ላይ ባተኮረ የግብርና ማዘመን ሥራን እንዲሁም በኢኮኖሚ እና ዘላቂ የመሠረተ ልማት ጉዳዮችን ያካተተ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከቡድን 20 ጉባኤ ጎን ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር የባለብዙ ወገን ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ብሎም እንደ የአየር ንብረት ጥበቃ ሥራ፣ ሰላም እና ፀጥታ፣ ዘላቂ ልማት ያሉ የጋራ አለምአቀፋዊ ትኩረቶችን በሚጠናከከሩበት መንገድ ላይ ተወያይተዋል። ኢትዮጵያ የCOP32 አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ ሊደረግ ስለሚችለው ድጋፍም ተወያይተዋል። እንዲሁም የኢትዮ-አውሮፓ ኅብረት ግንኙነት ለማላቅ ከአውሮፓ ኅብረት ምክርቤት ፕሬዝደንት አንቶኒዮ ኮስታ ጋር በተለያዩ ዘርፎች ትብብሮችን የበለጠ ለማጠናከር ተስማምተዋል። በተመሳሳይ የሁለትዮሽ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከካፍ ፕሬዝደንት ከዶክተር ፓትሪስ ሞትሲፒ እና ከአለም ባንክ ፕሬዝደንት አጄይ ባንጋ ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።

ከማሌዢያ እና ሲንጋፖር መሪዎች ጋር የተደረገ ዲፕሎመሲያ ውይይት

በዚሁ ህዳር ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የማሌዢያውን ፌደሬሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂምን እና የሲንጋፖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግን በብሔራዊ ቤተመንግሥት ይፋዊ የአቀባበል እድርገውላቸዋል። ሁለቱም ጉብኝቶች የችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓትን፣ የቤተ መንግሥት ሙዚየም ጉብኝቶችን እና የሁለትዮሽ ውይይቶችን ያካተቱ ናቸው። ኢትዮጵያ እና ሲንጋፖር በክህሎት ስልጠና እና በካርቦን ንግድ ላይ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ እና ማሌዥያ ደግሞ ቱሪዝምን፣ ጤናን፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እና የከተማ ትብብርን የሚመለከቱ ሰነዶችን ተፈራርመዋል። እነዚህ ጉብኝቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከደቡብ ምሥራቅ እስያ ጋር እያደገ የመጣውን ትብብር አጉልተው አሳይተዋል።

ለኮፕ 32 ዝግዘጋጀት የኢትዮጵያ መመረጥ

ኮፕ 32 የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑትን ጌዲዮን ጢሞቴዎስን (ዶ/ር) ፕሬዚዳንት አድርጎ መመደቡን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት ቁልፍ የዝግጅት ተግባራትን ለማቀናጀት የሚያስችል የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ስብሰባ ተደርጓል። ስብሰባው ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን ስታስተናግድ አካታች እና በሚገባ የተሰናዳ ጉባኤ እንድታሳካ ለማረጋገጥ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነበር።

በጥቅሉ በጥቅምት እና ሕዳር ወር 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን፣ የቱሪዝም ልማት ስራዎችን እና ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትግበራን ለማሳለጥ እንዲሁም ሀገሪቱን በዲፕሎማሲ ከፍ ለማድረግ የተከተሉት አመራር በውጤት የታጀበ ነበር። በወሩ መጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ እዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰንን አግኝተው በቀጠናዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርዋል።

#PMOEthiopia

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.