Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ የምክክር ጉባዔ ለመጥራት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ጉባዔው የሚመክርባቸውን አጀንዳዎች ቀርጾ ይፋ ለማድረግና ጉባዔውን ለመጥራት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው አሉ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)።

ኮሚሽኑ ”የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ምክክሩን ሁሉን አሳታፊና አካታች ለማድረግ ኮሚሽኑ ለተሳታፊ ልየታ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ የኃይማኖት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ጨምሮ በርካታ ተቋማትና ማህበራትን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም መንግሥትን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ማካተትና ማሳተፍ መቻሉንም ገልጸዋል።

በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰንም የዳያስፖራ ወገኖቻችንም በሂደቱ እንዲሳተፉ ጥረት ተርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኮሚሽኑ አሁን ላይ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው የሚመክርባቸውን አጀንዳዎች ቀርጾ ይፋ ለማድረግና ጉባዔውን ለመጥራት ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ወደዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ለመሸጋገር መከናወን ያለባቸው ወሳኝ ቀሪ ተግባራት አሉ ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ የትግራይ ክልል ሕዝብና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጀንዳቸውን የሚሰጡበትና በምክክር ጉባዔው ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ቀጣይ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ከመሳተፍ የታቀቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሂደቱ እንዲመጡ ለማድረግ ተጨማሪ ጥረቶችን ማድረግ ማስፈለጉንም አንስተዋል።

በተጨማሪም መሳሪያ አንግበው የሚቀሳቀሱ ቡድኖች ያሏቸውን አጀንዳዎች ወደ ምክክሩ አምጥተው መሳተፋቸው ለምክክሩ ሂደት ውጤታማነት ተጨማሪ አቅም በመሆኑ ልዩ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል።

የኃይማኖት ተቋማት አባቶች፣ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መፍትሔ በማፍለቅ ረገድ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.