የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የወል ትርክትን ለማስረጽ ሚናው ጉልህ ነው – አፈ ጉባዔ አገኘሁ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የወል ትርክትን ለማስረጽ ሚናው ጉልህ ነው አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፡፡
በአማራ ክልል በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር የቆየው 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ማጠቃለያ መርሐ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል፡፡
አፈ ጉባዔ አገኘሁ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የሕዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመንግስት የልማት ዕቅዶች እና ብሔራዊ ጥቅሞች በኢትዮጵያዊያን የተባበረ አንድት ለማሳካት ይሰራል፡፡
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ሕዝቦች ማንነታቸው እንዲከበር፣ ለፍትሕ፣ ነፃነትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት መከበርና መረጋገጥ በጋራ ጠንክረው እንዲሰሩ ማስቻሉን አመልክተዋል፡፡
እንዲሁም በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ሕብረብሄራዊ አንድነት እንዲጠናከርና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እንዲጎለብት መሰረት የጣለ ነው ሲሉም አውስተዋል።
በተለይም የለውጡ መንግስት በዓሉ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን እንዲያጎለብት፣ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብን እንዲያጠናክርና ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር እንዲሰብክበት እንዲሁም የወል ትርክት እንዲሰረጽበት መስራቱን አመልክተዋል፡፡
አበበ የሸዋልዑል