ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የምታሰራጨው መሰረት ቢስ ውንጀላ የክፍለ ዘመኑን እውነት ካለመረዳት ይመነጫል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የምታሰራጨው መሰረት ቢስ ውንጀላ የ21ኛውን ክፍለ ዘመን እውነት ካለመረዳት የመነጨና ተቀባይነት የሌለው ነው አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡
ሚኒስቴሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ÷ግብጽ የሁለትዮሽ ድርድሩን ወደ ጎን በመተው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ ላይ የምታሰራጨው መሰረት ቢስ ውንጀላ ተቀባይነት የለውም፡፡
በግብጽ መንግስት በኩል ኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች የ21ኛውን ክፍለ ዘመን እውነታ ካለመረዳት የሚመነጩ ናቸው ሲል አስገንዝቧል፡፡
የግብጽ ባለስልጣናት በቅኝ ግዛት ዘመን በነበረው አስተሳሰብ ላይ በመቸንከር በዓባይ ወንዝ ላይ የበላይነት አለን የሚል የተሳሳተ እሳቤ ማራመዳቸውን እንደቀጠሉ መግለጫው አመልክቷል፡፡
ካይሮ በተለይም ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና መረጋጋት እንዳይችል ከጸረ ሰላም ሃይሎች ጋር በቅንጅት እየሰራች እንደምትገኝ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
በግብጽ በኩል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አርቆ ካለማሰብ የመነጨና የከሸፈ ሃሳብ መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ ÷ መሰል ጊዜ ያለፈበት አካሄድ ኢትዮጵያ ላይ ምንም አይነት ለውጥ እንደማያስከትል አስገንዝቧል፡፡
በጸረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ፈር ቀዳጅ የሆነችው ኢትዮጵያ ግብጽ ከዓባይ ወንዝ ጋር ተያይዞ ለምታስበው የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት ቦታ እንደሌላት ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ ያለን የተፈጥሮ ሃብት ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልጋትም ያለው መግለጫው ÷ ይህን ስታደርግም የዓለም አቀፍ ሕጉን ተግባራዊ በማድረግ ነው ብሏል፡፡
ግብጽ ድርድር እና የጋራ ተጠቃሚነት መርሕን በመግፋት አግባብ ያልሆነ ትርክት ለመፍጠር የምታከናውነው እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም ሲል አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ ለጋራ ተጠቃሚነትና ብልጽግና እንዲሁም ለቀጣናዊ እድገት በቁርጠኝነት መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አብራርቷል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ እድገትና ትስስር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመልክቷል፡፡