Fana: At a Speed of Life!

ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ የመንግስትና የግል ዘርፉ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ መንግሥት በዘርፉ ከተሰማሩ የግል ተቋማት ጋር በቅንጅት ሊሰራ ይገባል አሉ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ምሁራን።

በወራቤ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ መሐመድ ኢሣ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ማድረግ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታል።

ዘመናዊና ቀልጣፋ የዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት ግልጽነትን እንደሚያሳድግ፣ ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት እንዲኖር እንደሚያግዝ ገልጸው፤ የንግድ፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ዘርፎችንም ለማሳለጥ ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የግል ተቋማት ዘርፉን የሚያሳድጉ የመፍትሄ ሀሳቦችን በማምጣት የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር በመደገፍ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

መንግሥት የግል ዘርፉ የሚጠበቅበትን ማበርከት እንዲችል ጠንከር ያለ ድጋፍ፣ ክትትል እና በመሠረተ ልማት የተደራጀ ምቹ ከባቢ እንዲፈጠር መስራት ይኖርበታል ነው ያሉት።

የቪዛ ምስራቅ አፍሪካ እና የቪዛ ኢትዮጵያ ኃላፊ ያሬድ እንዳለ በበኩላቸው፤ መንግሥት የዲጂታል ኢኮኖሚው ሽግግሩን እውን ለማድረግ የሚያከናውነው ተግባር ለግል ዘርፉ ምቹ ምሕዳርን እየፈጠረ ነው ብለዋል።

አዳዲስ ፖሊሲዎችን በማውጣት እና በማሻሻል የግሉ ዘርፍ ተሳታፊነት እና ተወዳዳሪነት ማሳደጉን ገልጸው፤ በተለይም የዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ መደረጉ ለዘርፉ እድገት አይነተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

መንግሥት ከግል ተቋማት ጋር በቅንጅት የሚሰራቸው ስራዎች መጠናከር አለባቸውም ብለዋል።

እንደ ሀገር እድገትን ለማፋጠን ሁሉንም ዘርፎች ዲጂታላይዝ ማድረግ እንደሚገባ እና በተለይም በፋይናንስ ዘርፉ የሚሰራው ስራ የሀገርን ኢኮኖሚ እድገት ለመከታተል ብሎም ተገማች እንዲሆን ያደርጋል ያሉት ደግሞ የአሪፍ ፔይ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ረድዔት ጽጌብርሃን ናቸው።

ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ የጀመረችው ስራ በፈጣን እድገት ላይ እንደሚገኝ እና ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 19 ትሪሊየን ብር በዲጂታል የፋይናንስ መንገዶች የገንዘብ ዝውውር መከናወኑን አስታውሰዋል።

ዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማፋጠን በዘርፉ የተሰማሩ የግል ተቋማት አበርክቶ ትልቅ እንደሆነ ጠቅሰው፤ መንግሥት ከግል ተቋማት ጋር በመቀናጀት አበረታች ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.