አርባ ምንጭና አካባቢዋን በቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ለማድረግ …
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕድን ሚኒስትር እና የገበታ ለሀገር አርባ ምንጭ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) አርባ ምንጭና አካባቢዋን በቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ አሉ።
አርባ ምንጭ ግንባታው እየተፋጠነ ያለውን የገበታ ለሀገር አርባ ምንጭ ሪዞርት ፕሮጀክትን ከባለሀብቶች ጋራ ማልማት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሂዷል።
ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ የገበታ ለሀገር አርባ ምንጭ ሪዞርት ግንባታ እየተገባደደ ነው።
በመሆኑም የአካባቢው ባለሀብቶች በትብብርና በጣምራ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንዳለ ጠቁመው፤ ዕድሉን እንዲጠቀሙበት አመላክተዋል።
መንግሥት አርባ ምንጭ ከተማንና አካባቢዋን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚሰራቸው ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመድረኩ የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ አልሚ ባለሃብቶች እንዲሁም የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው የገበታ ለሀገር አርባ ምንጭ ሪዞርት ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ግንባታው እየተፋጠነ ሲሆን በቅርብ ወራት ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።