Fana: At a Speed of Life!

የካሜሩን ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮ ቴሌኮም እና ካምቴል መካከል የተደረሰውን የአጋርነት ስምምነት አደነቁ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የካሜሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ዲዮን ንጉቴ (ዶ/ር) በኢትዮ ቴሌኮም እና ካምቴል መካከል የተደረሰውን የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት አድንቀዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ከካሜሩን ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከካምቴል ዋና ዳይሬክተር ጁዲት ያህ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው ጆሴፍ ዲዮን ንጉቴ (ዶ/ር)÷ ዲጂታላይዜሽን ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት መሆኑን አንስተዋል።

ዲጂታላይዜሽን ግቡን እንዲያሳካ የአፍሪካ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም እና ካምቴል በካሜሩን የዲጂታል ሽግግርን ለማፋጠን የደረሱትን የአጋርነት ስምምት አድንቀው÷ ኢትዮጵያና ካሜሩን በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ያላቸው አጋርነት እንዲጠናከር መንግሥታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ አድርገዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በሀገር አቀፍ ደረጃ ትስስሩን በማስፋት፣ ተደራሽነቱን በማረጋገጥ እና የፋይናንስ አካታችነትን በማፋጠን በኩል ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም እና የካሜሩን ቴሌኮሙኒኬሽን (ካምቴል) በትናንትናው እለት በካሜሩን የዲጂታል ሽግግርን ለማፋጠን የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.