የጉባ ብስራት ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ልዕልና የማረጋገጥ ጥረት ማሳያዎች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የጉባ ብስራት ግዙፍ ፕሮጀክቶች የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ልዕልና ለማረጋገጥ እንደሚተጋ ማሳያ ናቸው አሉ።
‘የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች’ በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ለመድረኩ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሃሳብ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሰው ተኮርና ግዙፍ የልማት ስኬቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
በመደመር መንግሥት የተፈጸሙ አስደናቂ የልማት ስኬቶች የመዲናዋንና የኢትዮጵያን ብልጽግና መፃኢ ዕድል የተሻለ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኮሪደር ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ኑሮ ውድነት ቅነሳ እና በመልካም አስተዳደር ማሻሻያ መርሃ ግብሮች መዲናዋን የሚመጥን ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።
የተገኙ ስኬቶችን ህዝብን ባሳተፈ አሰራር ቀጣይነት ላለው ዕድገት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የሕዝባዊ ውይይቱ ተሳታፊዎች፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የመልማት ፍላጎት የሚያሳኩ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በክፍለ ከተማው የመንገድ መሰረተ ልማትን ጨምሮ የህዝብን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ የሰጡ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የውሃ፣ የመብራት፣ የገበያ ማረጋጋት፣ የትውልድ ግንባታና የአገልግሎት አሰጣጥ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፤ የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ልዕልና ለማረጋገጥ እንደሚተጋ የሕዳሴ ግድብ ስኬትና የጉባ ብስራት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በቀጣይም ህዝብ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የኢንዱስትሪ ማዕከል የሆነው የአቃቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ላነሷቸው የመብራት፣ የውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ አወጋገድ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፤ የመደመር መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከህዝብ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በዚህም በዜጎች ቁርጠኛ ተሳትፎ በተለያዩ ዘርፎች የሀገርን ዕድገት የሚያሳልጡ እመርታዊ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በማዳመጥ በየጊዜው ምላሽ ለመስጠት እያደረገ ያለው ጥረትን አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
ሀገር የምትገነባው በተባበረ ክንድ በመሆኑ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ተሳትፎና አሻራ ወሳኝ ሚና አለው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞም መንግሥት በየዓመቱ በሚሊዮን ለሚልቁ ዜጎች በተለያዩ አማራጮች የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ካለፍ ፍላጎት አኳያ ቀጣይነት ያለው ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።