Fana: At a Speed of Life!

የትኛውም ትንኮሳና ክፉ ሃሳብ ኢትዮጵያን ከብልጽግና ማቆም አይችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትኛውም ትንኮሳ፣ ፈተናም ሆነ ክፉ ሃሳብ ኢትዮጵያን ከብልጽግና ማቆም አይችልም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሆሳዕና ከተማ እየተከበረ በሚገኘው 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት ቢሆንም በእጅጉ ልንጠቀምባቸው የሚገቡ ያልተነኩ እምቅ አቅሞች እንዳሏት አውስተዋል፡፡

ብልጽግናን ማሳካት ፈታኝ ሒደት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የወረስነው ነጻነት ብቻ ሳይሆን የተሸከምነውን የትውልድ አደራ ማሰብ ይኖርብናል፤ ብልጽግናን ለማጽናትም ሁሉም ተግቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን ችግር ብቻ ሳይሆን አቅሟን ፈልፍሎ የማየትና የማውጣት ብቃት እንዳለው ከጅምር ሥራዎች ማየት እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡

ብዙ እጆች በትብብር ካልሰሩ እህል ዳቦ እንደማይሆን ጠቁመው ÷ በትብብር መንፈስ በብዙ ልፋትና ትጋት በመስራት ዳግም ዓድዋን በኢትዮጵያ መዘከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብልጽግና እና ምልዑነት የሚጓደለው ኢትዮጵያውያን በሕብረት፣ በትጋትና በመተሳሰብ መስራት ካልቻሉ ብቻ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ይህን በመገንዘብ ሕብረ ብሔራዊነትን ማጠናከር፣ ገዢ ትርክትን ማስረጽ እንዲሁም በተቋማዊ ለውጥ የሀገረ መንግሥት ማጽናት ጅማሮን በማጎልበት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

በብቃትና ጥበብ እየሰራን የተዋበች፣ የላቀች፣ የጸናችና የበለጸገች ሀገር ለልጆቻችን ለማስረከብ ዛሬ የተሰጠንን ታላቅ እድል ልጠቀምበት ይገባል ብለዋል፡፡

አንድ ክር ደካማ ነው፤ ብዙ ክር ግን የማይበጠስ ገመድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ስንበዛ እና ስንሰናሰል በቀላሉ የማንበጠስ ገመድ ስለምንሆን ብሄራዊ ጥቅምን ማስቀደም የሁላችንም ሃብትና ስንቅ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የሀገርን መሻትና የባዳን ክፋት መለየት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ÷ ባዳ በክፋት የእኛን ሥራ ለማጨለም ሲነሳ ኢትዮጵያውያን ለባዳ ፍላጎት መሳሪያ መሆን የለብንም፤ ምክንያቱም በባዳ የተጠለፈ ገመድ አይፈታም አያስርም ሲሉ አስገንዝበዋል።

ክፉ እሳቤ ያለውን የባዳን መሻት ወደ ጎን በመተው በታሪክ ተወቃሽ እንዳንሆን ኢትዮጵያውያን ቀልብ ገዝተን ሰላማችንን እናጽና ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በንግግር እንመን፣ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ሁሉ በትጋት እንስራ፣ ሌብነትን እንጠየፍ፣ የሀገርን ጥቅምና የዜጎቻችንን ክብር እናስቀድም ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

ኢትዮጵያ በብዙ ተስፋ የተሞላች፤ አስደናቂ ጅማሮ እና ውጤት እያሳየችና እያንሰራራች የምትገኝ ሀገር መሆኗንም አውስተዋል።

ይህን መልካም ጅማሮ በሰይጣን ትጋት ቀን ከሌት ለማደናቀፍ ሙከራዎች እንደሚደረጉ ጠቅሰው ÷ ይሁን እንጂ ማንኛውም ፈተና፣ ትንኮሳና ክፉ ሃሳብ ኢትዮጵያን ከብልጽግና ማቆም አይችልም ብለዋል፡፡

እያንዳንዱን ፈተና ወደ እድል በመቀየር የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን፤ የኢትዮጵያን አንድነት እናጠናክራለን፤ የኢትዮጵያን ጠላቶች አንድ በአንድ እናራግፋለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.