ከባህልና ሥነ ምግባር ባፈነገጠ አስነዋሪ አለባበስ ለሕዝብ የታዩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሀገራችን ባህልና ሥነ ምግባር ያፈነገጠ አስነዋሪ አለባበስ ለብሰው በአደባባይና በቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት ለሕዝብ የታዩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ዋሉ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በ3ኛው የጂ ፓወር ቲክቶክ ክሬቲቭ አዋርድ ላይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባህልና ሥነ ምግባር ባፈነገጠ አኳኋን ሰውነታቸውን የገላለጠ አለባበስ ለብሰው በአደባባይና በቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት ለሕዝብ መታየታቸውን የፌደራል ፖሊስ ገልጿል፡፡
ፖሊስ እነዚህን ግለሰቦች እንዲሁም ዝግጅቱን በስፖንሰርነት የደገፉና ፕሮግራሙን ያቀነባበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት ወንጌላዊት ገብረ እንድርያስ፣ በርከት ፀጋዬ፣ መቅድም ደረጀ፣ ግሩም ገዛኸኝ እና ዮሃንስ መኮንን የተባሉ ግለሰቦች መሆናቸውን ገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ ከህብረተሰቡ ባህልና እሴት ያፈነገጡ አለባበሶችና መጤ ባህሎች ተስፋፍተው በትውልዱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያስከትሉ ተጠርጣሪዎቹ ላይ የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የጀመረውን ምርመራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል፡፡