Fana: At a Speed of Life!

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው – አቶ አወሉ አብዲ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአስተራረስ ባህልን ከዝናብ ጠባቂነት በማላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው አሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ።

አቶ አወሉ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን የመኸር ምርት አሰባሰብና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት÷ የአስተራረስ ባህልን ከዝናብ ጠባቂነት በማላቀቅ አርሶ አደሮች ዓመቱን ሙሉ አንዲያመርቱና ለገበያ እንዲያቀርቡ ማድረግ ተችሏል።

ይህም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ከማረጋገጥ ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ስለመሆኑ አመላካች ብለዋል።

የአስተራረስ እና የገበያ ባህልን በመቀየር ከእጅ ወደ አፍ የነበረውን የአምራችነት ታሪክ መቀየር መቻሉንም ተናግረዋል።

በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የሚታረስ የመሬት ሽፋንን ማሳደግ፣ ባሉ መሬቶች ላይ ምርታማነትን መጨመር፣ ሜካናይዜሽንን ማስፋፋትና የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ግንዛቤ በማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆን መጀመራቸውን አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም በሄክታር በአማካይ ይገኝ የነበረው የምርት መጠን ከ15 እስከ 20 ኩንታል እንደነበር አስታውሰው÷ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት በሄክታር ከ30 እስከ 40 ኩንታል ምርት መሰብሰብ መጀመሩን ጠቁመዋል።

አምራቹ በተመጣጣኝ ክፍያና በብድር አገልግሎት የሜካናይዜሽን ግብዓቶችን እንዲያገኝ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በመኸር እርሻ 590 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች የተሸፈነ ሲሆን÷ 85 በመቶው በመካናይዜሽን ታግዞ የለማ እንደሆነና ከዚህም 11 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገልጿል።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.