የኮፕ32 እና የኢንተርፖል ጉባኤዎች በስኬት እንዲከናወኑ የሚያስችል ዝግጅት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው የኮፕ32 እና የኢንተርፖል ጉባኤዎች በስኬት እንዲከናወኑ የሚያስችል ዝግጅት ይፋ ተደርጓል።
ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ32)፣ 96ኛውን የኢንተርፖል ጠቅላላ ጉባኤ እንዲሁም 27ኛውን የኢንተርፖል የአፍሪካ ቀጣና ኮንፈረንስ ለማዘጋጀት መመረጧ ይታወሳል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ጉባኤዎቹ በስኬት እንዲከናወኑ የሚያስችለውን ዝግጅት ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች በተገኙበት በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ዝግጅቱን የሚመራ የፖሊስ ኃይል የተደራጀ ሲሆን፥ የዝግጅት ስራዎቹ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይከናወናሉ፡፡
ጉባኤዎቹ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ እንዲካሄዱ ለማስቻል ሁለንተናዊ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ በስፋትና በጥራት እንዲዘጋጁ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ተጨማሪ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችና ትጥቆችን በማደራጀት ሰፊ የሎጂስቲክስና የቴክኖሎጂ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ የመገንባት ስራዎች እንዲሰሩም ነው ያሳሰቡት፡፡
የኢትዮጵያን ፖሊስ ታሪካዊ ዳራ የሚያሳይ አውደ ርዕይ የማዘጋጀት፣ የፖሊስ ለፖሊስ የውጭ ግንኙነትና የትብብር ሥራዎችን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል፡፡