በመዲናዋ የተካሄደው ሕዝባዊ ውይይት ለሕዝብ ጥያቄዎች በተግባር የተደገፈ ማብራሪያ የተሰጠበት ነው – አቶ ሃፍታይ ገ/እግዚአብሔር
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተካሄደው ሕዝባዊ ውይይት ለሕዝቡ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ የተሰጠበት ነው አሉ የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገ/እግዚአብሔር።
ኃላፊው “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ሐሳብ ባሳለፍነው ቅዳሜ በመዲናዋ የተካሄደውን ሕዝባዊ ውይይት አስመልክቶ ከፋና ፖድካስት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በስራ አስፈፃሚ ደረጃ የተመሩ ውይይቶች ሕዝቡ ለተሰሩት ስራዎች አድናቆቱን የገለጸበትና በቀጣይ ለሚሰሩ የልማት ስራዎች በንቃት እንደሚሳተፍ ያረጋገጠበት መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ያነሱት አቶ ሃፍታይ÷ በ2018 ዓ.ም ባለፉት 3 ወራት ብቻ 40 ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ኮንፈረንሶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህም መዲናችን በከፍተኛ የለውጥ ጎዳና ላይ እንደሆነች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየመሰከረ ስለመሆኑ አመላካች ነው ብለዋል፡፡
የከተማዋ ሁለንተናዊ እድገትና የዓለም የስበት ማዕከል መሆን ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ሕብረተሰቡ በከተማዋ እድገት ተጠቃሚ እንዲሆን ከሕዝብ ጋር መወያየቱ አስፈላጊ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ሕዝባዊ ውይይቱ በሁሉም የመዲናዋ ክፍለ ከተሞች የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች በተገኙበት መካሄዱንም ጠቁመዋል።
በአመለወርቅ ደምሰው
አቶ ሃፍታይ ገ/እግዚአብሔር ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ በተከታዩ ማስፈንጠሪያ ይከታተሉ👇
https://www.youtube.com/watch?v=iJjQMhjrWXg