ኢትዮጵያና ዛምቢያ በወታደራዊ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ዛምቢያ በወታደራዊ መስክ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከዛምቢያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናል ጄነራል ጄፍሪ ዚኤሌ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚህ ወቅት ÷ ለቀጣናው ደኅንነት እንዲሁም ለሀገራት ሠላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ተናግረዋል፡፡
ከዛምቢያ ጋራ ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ እንደሚሠራም ነው አጽንኦት ሰጡት።
ሌተናል ጄነራል ጄፍሪ ዚኤሌ በበኩላቸው ÷ ወታደራዊ ትብብሩ የተሻለ አቅም ለመፍጠርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደሚግዝ አስረድተዋል፡፡
ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ ያለውን የኢትዮጵያን ሠራዊት ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም የኢትዮጵያዊያንን የጀግንነት ሥነ ልቦና ያደነቁት ሌ/ጄ ጄፍሪ ዚኤሌ÷ ይህም ብዙ የተማርንበትና በትብብር እንድንሰራ ያነሳሳን ነው ብለዋል።
ኤታማዦር ሹሙ በልዩ ልዩ ወታደራዊ መስኮች በጋራ ለመሥራት ዛምቢያ ያቀረበችውን ጥያቄ ኢትዮጵያ በመቀበሏ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ውይይቱን ተከትሎ የመከላከያ ሚኒስትር ዴዔታ ማርታ ሉዊጂ ከዛምቢያ አቻቸው ማምቦ ሃማውንዱ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመነዋል፡፡
ስምምነቱ ሀገራቱ በዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ፣ በደኅንነት፣ በወታደራዊ ትምህርትና ሥልጠና፣ በወታደራዊ ኢንዱስትሪና በሌሎች ዘርፎች በጋራ መሥራት የሚያስችል መሆኑን የመከላከያ ሠራዊት ኦንላይን ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ሌ/ኮ ውብሸት ቸኮል ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።