Fana: At a Speed of Life!

በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት የሕዝብን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የሰላም አማራጭን ሊቀበሉ ይገባል – የአፋሕድ ከፍተኛ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት የሀገርና ሕዝብን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የሰላም አማራጭን ሊቀበሉ ይገባል አሉ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች።

በአማራ ክልል መንግሥትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች መግለጫ ሰጥተዋል።

የአፋህድ ም/የፖለቲካ መምሪያ ኃላፊና የወሎ ቤተ አማራ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ እያሡ አበራ ፥ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ በትጥቅ ትግል እናስከብራለን በሚል በጫካ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል መንግሥትና በሕዝባዊ ድርጅቱ የተፈረመው የሰላም ስምምነትም የአማራን ሕዝብ ክብርና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባከበረ መንገድ የተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።

የተፈረመው የሰላም ስምምነትም በዘፈቀደ የተመራ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው መንገድ መፈጸሙን ነው ያስረዱት፡፡

የአማራ ሕዝብ ከዚህ በላይ ጦርነትን የመሸከም አቅም የለውም፤ሌሎች በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላትም የሕዝብና የሀገርን ጥቅምና ክብር በሚያስከብር አግባብ የሰላም አማራጭን መቀበል አለባቸው ብለዋል።

በዚህም ለሕዝብ የሚበጅ ትክክለኛ የንግግር ውሳኔን በማሳለፍ የሰላም አማራጭ መምረጣቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይም የሀገርና ሕዝብን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት በማስጠበቅ ከክልሉና ፌደራል መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የፋይናንስ ኃላፊ ከፋለ አለሙ በበኩላቸው ፥ ከዓመታት በፊት ጀምሮ ዘላቂ ሰላምን ለማውረድ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ንግግር መደረጉን አስታውሰዋል።

በዚህም የተደረጉ ንግግሮች ፍሬ አፍርተው የዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈረሙ ሕዝብን፣ የድርጅቱን አመራርና የሠራዊት አባላት ያስደሰተ መሆኑን ገልጸዋል።

ከቀድሞው ሕወሓት፣ ሻዕቢያ እና ግብጽ ጋር የሚደረግ የጥፋት ተልዕኮም ለአማራ ሕዝብም ሆነ ኢትዮጵያ የሚጠቅም ባለመሆኑ የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን ተናግረዋል።

መርሕ የለሽ የትጥቅ ትግል ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው በማስቀረት ጫና እያሳደረ በመሆኑ ቀሪ በጫካ የሚገኙ የፋኖ አደረጃጀቶችም የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በትጥቅ ትግል የአማራ ሕዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉስቁልና እንዲያስተናግድ ተደርጓል ያሉት ደግሞ በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የወሎ ቤተ አማራ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የሕዝብ አስተዳደርና ማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ ግርማ እጅጋየሁ ናቸው፡፡

በዚህም ትክክለኛውን የሰላም አማራጭ በመከተል የተሄደበት የተሳሳተ የውክልና ጦርነት በመተው የሰላም ስምምነት መምረጣቸውን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.