ሙስናን የሚጠየፍ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሙስናን የመከላከል ትግልን ሁሉም ሕብረተሰብና ተቋማት በባለቤትነት ሊይዙት ይገባል አሉ፡፡
“ትውልድን በሥነ ምግባር፣ ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ሃሳብ 22ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በዛሬው ዕለት ተከብሯል፡፡
ከንቲባ አዳነች በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ብሔራዊ አጀንዳ አድርገን ያፋፋምነው የጸረ ሙስና ትግል ከዚህ ቀደም የነበረውን አስከፊ መንግሥታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት አስችሏል ።
ሙስና የብልፅግና ጸርና የኢፍትሃዊነት ምንጭ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ ፥ ዓለም አቀፉን የጸረ ሙስና ቀን ስናከብር ሙስናን ለመዋጋት ያለንን ቁርጠኝነትና የገባነውን ቃል በማደስ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር ብሎም በመዲናዋ የሕዝብና የመንግሥትን ሃብት በተገቢው የልማት ሥራዎች ላይ በማዋላችን አስደናቂ የልማት ውጤቶች ማሳየት ችለናል ነው ያሉት።
መንግሥታዊና ሥርዓታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት መቻሉን ጠቅሰው ፥ በግለሰብ ደረጃ በመንግስት ኃላፊዎችና ሰራተኞች የሚፈፀመው ሌብነትና ጉበኝነት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ ጠቁመዋል፡፡
ለሙስና አጋላጭ አሰራሮችን ለመዝጋትና ከምንጩ ለማድረቅ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን በማጠናከር፣ መንግስታዊ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን በተሟላ መልክ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሒደት ቤተሰብ፣ ማሕበረሰቡ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት ተቋማትና የሲቪክ ማህበራትን ጨምሮ የሁሉም ተቋማት ትግልና የኅብረተሰቡ ከፍተኛ ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የፀረ ሙስና ትግሉ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው፥ በአመለካከትም በተግባርም ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡