ለ24 ነጥብ 8 ሚሊየን ህፃናት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ይሰጣል – ዶ/ር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዚህ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ24 ነጥብ 8 ሚሊየን ህፃናት የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት ይሰጣል አሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፡፡
ሚኒስትሯ ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻን በዛሬው ዕለት በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ አስጀምረዋል።
ፖሊዮ አሁንም የዓለም ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ያሉት ሚኒስትሯ፥ የህጻናትን የወደፊት እጣ ፈንታ ለማስቀጠል ፖሊዮን ማጥፋት የግድ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ24 ነጥብ 8 ሚሊየን ህፃናት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ ገልጸው፥ አስፈላጊው ቁሳቁስ ወደ ክልሎች ተጓጉዞ ክትባት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን በሰባት ክልሎች በተደረገው የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከ8 ሚሊየን በላይ ህጻናት ተከትበዋል ያሉት ሚኒስትሯ፥ የክትባት ዘመቻው እንዲሳካ ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህፃናት በሙሉ መከተብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ በበኩላቸው፥ የፖሊዮ ክትባትን ለማዳረስ በክልሉ ሁሉም ዞኖች ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
በጥላሁን ይልማ