በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ16ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ቼልሲ በስታምፎርድ ብሪጅ ኤቨርተንን የሚያስተናግድ ሲሆን÷ ባለፉት ሶስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ያለማሸነፍ ጉዞውን ለመግታት ይጫወታል፡፡
ያለፉት ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በማሸነፍ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘው ኤቨርተን ለቼልሲ ከባድ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በተመሳሳይ ሰዓት ሊቨርፑል በአንፊልድ ብራይተንን የሚያስተናግድ ሲሆን÷ ሞሃመድ ሳላህ በስብስቡ ተካትቷል፡፡
የአንፊልዱ ግጥሚያ ለግብጻዊው ኮከብ የመጨረሻ ጨዋታ እንደሚሆን ተገምቷል፤ በጫወታው እድል የማግኘቱ ጉዳይም ይጠበቃል፡፡
በሊጉ ደካማ እንቅስቃሴን እያደረገ የሚገኘው ሊቨርፑል በሳምንቱ አጋማሽ በሻምፒዮንስ ሊግ ኢንተርሚላንን ማሸነፉ ጥሩ መነቃቃት እንደሚፈጥርለት ተመላክቷል፡፡
ምሽት 2 ሰዓት ከ30 በርንሌይ ከፉልሃም ሲጫወቱ በሌላ በኩል አርሰናል ከወልቭስ ምሽት 5 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
መድፈኞቹ ከ18 ተከታታይ ያለመሸነፍ ጉዞ በኋላ ባለፈው ሳምንት በአስቶንቪላ መሸነፋቸውን ተከትሎ ከማንቼስተር ሲቲ በሁለት ነጥብ ብቻ በመራቅ ሊጉን እየመሩ ይገኛሉ፡፡
በሊጉ ባደረጓቸው 15 ጨዋታዎች በ13ቱ የተሸነፉት ወልቭሶች ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይጫወታሉ፡፡
በአቤል ነዋይ