Fana: At a Speed of Life!

 ሰላምን በማፅናት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው – ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰላምን በማፅናት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ ነው አሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፡፡

ከሁለቱ ዞኖች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በጀዋሃ ከተማ በሰላም እና ልማት ዙሪያ ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በመድረኩ እንዳነሱት፤ ፀረ ሰላም ሀይሎች በፈጠሩት የጥላቻ ዘመቻ ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ደርሷል።

አሁን ላይ መንግሥትና ማህበረሰቡ ባደረጉት የተቀናጀ ሰላም የማጽናት ተግባር የህብረተሰቡ ማህበራዊ መስተጋብር እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር መጠናከሩን ገልጸዋል።

ከሰላም ጥያቄ ወደ ልማት ፍላጎት ተሸጋግረናል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች÷ በጋራ የፈጠርነውን ሰላም አጽንተን እናስቀጥላለን ብለዋል፡፡

የአካባቢው የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረትም እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አህመድ አሊ÷ ሰውነትን በማስቀደም አብሮነት ላይ በመሰራቱ ከሰላም ወደ መልማት ጥያቄ መሸጋገር ተችሏል ብለዋል።

በቀጣይም አስተማማኝ ሰላም በመዘርጋት የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ÷ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ የመጣውን ሰላም ለማጽናት እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር ) በበኩላቸው÷ የአካባቢውን ጸጋ ወደ ልማት ለማስገባት እና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት እና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

በአካባቢው የመጣውን ሰላም በማጽናት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች በጠራ አመለካከት ለአንድነት እና አብሮነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በአለባቸው አባተ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.