ባለፉት ዓመታት ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ጥቂት ዓመታት ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል አሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)።
የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሐረሪ ክልል የገጠርና ከተማ ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በሐረር ከተማ ‘የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች’ በሚል መሪ ሃሳብ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) መድረኩ እንዳሉት፤ ውይይቱ የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ለማስቀጠልና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያግዛል።
እንዲሁም በህዝብና በመንግሥት መካከል መተማንን በማጎልበት የመንግሥትን የመፈፀም አቅም ለማሳደግ የላቀ ፋይዳ አለው በማለት ገልጸው፤ መድረኩ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስና የህዝብ ተሳትፎን ለማሳደግ ይረዳል ነው ያሉት።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመቅረፍ በስፋት መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህም ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝም እና የከተማ ልማትን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
መንግሥት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በሚያከናውነው ተግባር አጀንዳው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማስቻሉን ጠቅሰው፤ ከዚህ ባለፈም በርካታ የዲፕሎማሲ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት አሁን ላይ የሀገርን ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚያስችሉ መልኩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
በሀረሪ ክልል በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተመልክተናል ያሉት ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፤ በተለይም በከተማ ልማት ዘርፍ ምሳሌ የሚሆን ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተስፋዬ ኃይሉ