ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር አዲስ የሰላም ውይይት ልታደርግ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዩክሬን እና አሜሪካ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አዲስ የሰላም ውይይት ያደርጋሉ ተባለ።
አዲሱ የሰላም ውይይት በአሜሪካ የሚካሄድ መሆኑን ኬቭ ፖስት ዘግቧል።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እንዳሉት፤ ዋሽንግተን ከሞስኮ ጋር ያደረገችውን ምክክር እና በበርሊን የተካሄደውን ጠንካራ ድርድር ተከትሎ የዩክሬን እና የአሜሪካ የሰላም ሂደት ቡድኖች የሰላም እቅድ ላይ ሌላ ዙር ውይይት ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።
የአሜሪካ የሰላም ሂደት ቡድን ቀጣዩን የውይይት መድረክ የሚቀርጹ ሰነዶችን በማጠናቀቅ ላይ እንደሆነ የገለጹት ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ፤ ሰነዶቹ ዛሬ ወይም ነገ ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
ከዚያም አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ምክክር እንደምታደርግ ገልጸው፤ ይህ ከሆነ በኋላ የሰላም ውይይቱ በአሜሪካ እና በዩክሬን ቡድኖች መካከል ይካሄዳል ብለዋል።
አዲሱ የሰላም ውይይት ውጤት የአሜሪካ እና የዩክሬን የመሪዎች ደረጃ ስብሰባን ጨምሮ ቀጣይ ርምጃዎችን እንደሚወስን ገልጸዋል።
በጀርመን በርሊን ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በተካሄደው የሰላም ምክክር ላይ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ እና የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ መገኘታቸው ይታወቃል።
የአሜሪካ የሰላም ቡድን አባላት እንደገለጹት የበርሊኑ መድረክ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች የታዩበት እንደሆነም ገልጸው፤ የቡድኑ አባላት ከፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በተጨማሪ ከጀርመን፣ ከብሪታኒያ እና ከፈረንሳይ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መምከራቸውን አስታውቀዋል።
በሶስና አለማየሁ