ሕዝባዊ ውይይቶች ወቅታዊና ሀገራዊ ችግሮችን ለመለየትና መፍትሄ ለመስጠት…
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች መንግሥት ወቅታዊና ሀገራዊ ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ እንዲሰጥ ያግዛል አሉ ምሁራን፡፡
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ቢመርቅ በሪሁን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ ሕዝባዊ ውይይቶች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የገጠማትን የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶች ለመመከት ሕዝብን ያሳተፉ ውይይቶች መደረጋቸው ትልቅ ትርጉም እንዳላቸው አስረድተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የመልካም አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ይታገሱ በቀለ በበኩላቸው÷ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተደረጉ ውይይቶች መንግሥት ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት ግብዓት ያገኘበት ነው ብለዋል።
ውይይቶችን ከማድረግ ባሻገር በተለያዩ መድረኮች ከሕዝብ የተነሱ ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ ለመስጠት መንግሥት ቁርጠኛ ሊሆን እንደሚገባ ምሁራን አስገንዝበዋል።
ለተነሱ ጉዳዮች መፍትሄ መስጠት በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመንን ከመፍጠር ባሻገር ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚበያረክት አብራርተዋል፡፡
መንግሥት ከሰሞኑ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጋቸው ውይይቶች ችግሮችን ከሥሩ ለይቶ ለማወቅና መፍትሄ ለመስጠት ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
በተስፋዬ ምሬሳ