Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኦፓል ግብይት ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ‎የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኦፓልን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናትን ለማገበያየት የሚያስችል ዝግጅት አድርጌአለሁ አለ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መርጊያ ባይሳ እንዳሉት፤ ተቋሙ ግብይትን በማዘመንና በግልጽነት መርሆዎች በመምራት የሀገሪቱን የንግድ ሥርዓት ለማቀላጠፍ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

‎በበቆሎና ስንዴ ግብይት ስራውን የጀመረው ምርት ገበያው፤ በአሁኑ ወቅት ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመሞችን ጨምሮ የሚያገበያያቸውን የግብርና ምርቶች ወደ 28 ከፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

‌‎በተለይ ከለውጡ በኋላ መንግሥት በሰጠው ትኩረት 15 አዳዲስ ምርቶችን ወደ ግብይቱ ማስገባት መቻሉን ጠቅሰዋል።

‎ምርት ገበያው ተወዳዳሪና ተፈላጊ የግብይት መዳረሻ እንዲሆን በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተው፤ በዚህ ምርት ገበያው የበለጠ ውጤታማ እየሆነ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ ተቋሙ ከግብርና ውጭ የሆኑ ማዕድንና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማገበያየት የሚችልበት ኃላፊነት እንደተሰጠው ‎ዋና ‎ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል።

‌‎ይህንኑ ተከትሎ የኦፓል ማዕድንን ወደ ገበያ ለማስገባት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

‌‎ከኦፓል በተጨማሪ ሌሎች ማዕድናትን ለማገበያየት የሚያስችል ራሱን የቻለ የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት በምርት ገበያው በኩል ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ብለዋል።

በማዕድን ሚኒስቴር በኩል መጠናቀቅ ያለባቸው ጉዳዮች ሲፈጸሙ የማገበያየት ስራው እንደሚጀመር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የአርቴዝናል እና ጌጣጌጥ ማዕድን ልማት ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ጌራ ተጫነ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፍ የሚስተዋሉ የግብይት ችግሮችን ለመፍታትና ዘርፉን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይህንን ተከትሎ የኦፓልን ምርት የሚስተዋሉ የግብይት ችግሮችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር የተጀመረው ሥራ በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

‎ምርቱ በምርት ገበያ በኩል መቅረቡ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከልና አምራቾችን ይበልጥ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.