Fana: At a Speed of Life!

የመንግሥት ሰራተኞች እና ጡረተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጤና መድኅን ስርዓት ለመተግበር …

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥት ሰራተኞች እና ጡረተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የማህበራዊ ጤና መድኅን ስርዓት ለመተግበር እየተሰራ ነው አለ የኢትዮጵያ ጤና መድኀን አገልግሎት።

የኢትዮጵያ ጤና መድኀን አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ያምሮት አንዱዓለም ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ በ2017 ዓ.ም ከ13 ነጥብ 67 ሚሊየን በላይ ቤተሰብ በማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድኅን ተመዝግቦ አገልግሎት እያገኘ ነው።

የህብረተሰቡ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በየዓመቱ ለአገልግሎት የሚመዘገቡ አባላት ወቅቱን ጠብቀው አባልነታቸውን እያደሱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በዚህም የአባላት እድሳት ምጣኔ ከ96 በመቶ በላይ መድረሱን አመልክተዋል።

የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድህን ደመወዝተኛ እና የጡረታ አበል የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያካትት እንደሆነ አንስተው፤ በንግድ፣ በግብርና እና ሌሎች መስኮች ቋሚ ገቢ ሳይኖራቸው የሚተዳደሩትን የሚመለከት መሆኑን ገልጸዋል።

የጤና መድኅን ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለበት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

በመሆኑም የመንግሥት ሰራተኞች እና ጡረተኞችን የሚመለከተውን የማሕበራዊ ጤና መድኅን አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በህክምና ሥራ ላይ ለተሰማሩ ዜጎች የመጀመሪያው የሙከራ ትግበራ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

በሄኖክ በቀለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.