የወል ትርክቶችን መገንባት የሚያስችሉ ፕላትፎርሞች ተቀርጸው ወደ ሥራ ገብተዋል – የሰላም ማኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፋፋይ ትርክቶችን በማስወገድ የጋራ ትርክቶችን መገንባት የሚያስችሉ ፕላትፎርሞች ተቀርጸው ወደ ሥራ ገብተዋል አለ የሰላም ማኒስቴር።
“የትምህርት ማሕበረሰብ ለሰላም “በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ዴስክ ሃላፊ አቶ ወንድወሰን መኮንን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ኢትዮጵያ የምትመራበትን የሰላም ፖሊሲ ረቂቅ ከማዘጋጀት ጀምሮ የወል ትርክቶችን ማጉላት የሚችሉ አማራጮች ተዘርግተዋል።
ለሰላም ግንባታ ሥራዎች ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው÷ በመጀመሪያና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰላም አደረጃጀቶችን በማቋቋም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰላም ፎረሞችን በማደራጀት ተማሪዎች የሀገር ፍቅር ስሜትን እንዲረዱና ለሰላም ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
100 ሺህ ያህል በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሰላም ግንባታ ላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት በተለያዩ ክልሎች መሰማራታቸውን ነው ያስረዱት፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ዴስክ ሃላፊ አቶ ኡመር ይማም በበኩላቸው÷ የትምህርት ተቋማት ለሰላም አስፈላጊና ዋና መሳሪያ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰላምን ለማጽናት የትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ኃላፊው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን