ልዩ የኮማንዶ ኃይላችን አስቸጋሪ ኦፕሬሽኖችን በጀግንነት የሚፈጽም ነው – ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ልዩ የኮማንዶ ኃይላችን ልዩ እና አስቸጋሪ ኦፕሬሽኖችን በእውቀትና በጀግንነት የሚፈጽም ነው አሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በአካዳሚው ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ልዩ የኮማንዶ አባላትን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ዛሬ አስመርቋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በወቅቱ እንዳሉት፤ ተመራቂዎቹ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተመለመሉ ሲሆኑ፤ ላለፉት 16 ወራት ልዩ ፖሊሳዊ ስልጠና ወስደዋል።
በዚህ ልዩ የኮማንዶ ስልጠና ማናቸውንም ልዩ ኦፕሬሽኖች እና ግዳጆች መወጣት የሚያስችል ጠንካራ አቅም መፍጠራቸውንም ጠቅሰዋል።
ፖሊስ በሕግ፣ በአሠራር፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በውስጥና በውጪ ግንኙነት ስኬታማ ሪፎርም አካሂዷል ብለዋል።
በዚህም የሀገር አለኝታ የሆነ፣ ገለልተኛና ሙያዊ ብቃት እና የመፈጸም አቅም ያለው፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የፖሊስ ተቋም መገንባቱን ገልጸዋል።
በተለይም የሰው ኃይሉ ወቅቱ የሚፈልገውን የተሟላ ፖሊሳዊ እውቀት፣ ክህሎት እና ስብዕና እንዲላበስ የማሰልጠኛ ተቋማትን ማሳደግ ችለናል ነው ያሉት።
የፖሊስ ኃይሉ ባለፉት ጊዜያት በሀገር እና በሕዝቦቿ ላይ በባንዳ እና በባዳ የተቃጡ ሀገር የማፍረስ ሴራዎችን ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ማክሸፉንና ሰላምን ማረጋገጡን ገልጸዋል።
ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሰላምን ለማደናቀፍ እንደማይተኙ ጠቅሰው፤ ማናቸውንም ግዳጆች በብቃት እና በቁርጠኝነት ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ ነን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ እና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በስኬት ለማጠናቀቅ የፖሊስ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ መዘጋጀቱንም አረጋግጠዋል።
የልዩ ኮማንዶ ኃይሉ ተልዕኮ ብርታትን፣ ትዕግስትን፣ የመንፈስ ጽናትን፣ እምነትንና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው፤ ተመራቂዎች የተልዕኮውን ክብደት በመገንዘብ በስልጠና ወቅት ባሳዩት ብቃት፣ የአዕምሮ ጽናት፣ እውቀትና ክህሎት ሙያቸውን በብቃትና በቁርጠኝነት በተግባር እንዲወጡም አሳስበዋል።