በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የሳይበር ደህንነት ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ ነው – ወ/ሮ ትዕግስት ሀሚድ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ከመሰረተ ልማት እና ኃይል ቀጥሎ ስትራቴጂካዊ ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ ነው አሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ።
ዋና ዳይሬክተሯ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ እና አመኔታ የፈጠረ እንዲሆን ማስቻልን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ የሳይበር ደህንነት ስጋቶች ገጽታ በጣም ሰፊ፣ እያደገ የመጣ እና ለነገ ተብሎ የሚተው ጉዳይ አይደለም።
የዲጂታላይዜሽን ሥነ ምሕዳር እየሰፋ መምጣቱን እና የሳይበር ደህንነትን መጠበቅ መሰረት ሆኖ ሊዳሰስ እንደሚገባ ገልጸው ÷ቁልፍ የሚባሉ ሀገራዊ ተቋማቶችን በንቃት መጠበቅ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ዜጎች፣ ተቋማት እና አጠቃላይ ዲጂታል ኢኮኖሚው ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን መስራት እና ዲጂታል መተማመንን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የሳይበር ደህንነት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂክ ምሰሶ ሆኖ ሲሰራ መቆይቱን አስታውሰው ÷በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ቁልፍ የመሰረተ ልማት ጉዳይ ማሳካት እንደተቻለ እና ለሳይበር ደህንነቱ ቁልፍ የሆነ የክላውድ መሰረተ ልማት መገንባቱን ተናግረዋል።
እንዲሁም በቴክኖሎጂ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል ከህግ አስፈጻሚ አካላት በትብብር የሚሰራበት ዲጂታል ፎረንሲክ ላቦራቶሪ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸው፤ የሰው ኃይልን በማልማትም ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መደላድል የሚሆኑ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በአዲሱ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሳይበር ደህንነት ከመሰረተ ልማት እና ኃይል ቀጥሎ ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ወደ 47 የሚሆኑ ስትራቴጂክ ኢኒሼቲቮች ተቀርጸው ወደ ስራ መገባቱን ነው ያመላከቱት።
አይበገሬ የሆነ ቁልፍ መሰረተ ልማት መገንባት፣ የህዝብ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ማዘመን፣ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት አቅም እና የዘርፎችን ዝግጁነት ማጠናከር፣ የአደጋ ምላሽ መስጫ ማዕከሎችን ማቋቋም እና የግል ተቋማት በሳይበር ደህንነት ዘርፉ እንዲሰማሩ እድል መፍጠር የስትራቴጂው 5 ዋና ኢኒሼቲቮች እንደሆኑ አስረድተዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ሲሳካ የዲጂታል መተማመን እንደሚፈጠር፣ የዲጂታል ሉዓላዊነት እንደሚረጋግጥ እና የሳይበር ደህንነትን ከ95 በመቶ በላይ እንደሚደርስ አብራርተዋል።
ይህንን ለማሳካት በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የግንዛቤ ፈጠራ ንቅናቄዎች በማካሄድ፣ ለሳይበር ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት፣ በሳይበር ደህንነት ጉዳይ ላይ የሚወጡ አዋጆች እና መመሪያዎች ከመተግበር አንጻር ያሉ ክፍተቶችን በመቅረፍ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
በዮናስ ጌትነት