Fana: At a Speed of Life!

በ19 አመቱ የዓለም ዋንጫን ከሀገሩ ጋር ያነሳው ኪሊያን ምባፔ…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዚህ ትውልድ ምርጡ ተጫዋችና ከሀገሩ ጋር በ19 አመቱ የዓለም ዋንጫን ያነሳው ኪሊያን ምባፔ ሎቲን የተወለደው በፈረንጆቹ 1998 በፈረንሳይ ፓሪስ ነው፡፡

በፈጣን ሩጫዎቹ እና ድንቅ ግብ አስቆጣሪነቱ የሚደነቀው ኪሊያን ምባፔ የእግር ኳስ ህይወትን የጀመረው በፈረንጆቹ 2015 በሞናኮ ነበር፡፡

ከሞናኮ ጋር ገና በልጅነቱ በ2016/17 የውድድር ዓመት የሊግ አንድ ዋንጫን ያሳካው ምባፔ በ2017 በ18 አመቱ ለሌላኛው የፈረንሳይ ሀያል ክለብ ፒኤስጂ በ180 ሚሊዮን ዩሮ ፊርማውን ማኖሩ ይታወሳል፡፡

ክለቡ ለኪሊያን ያወጣው የዝውውር ሂሳብ ሁለተኛው ውድ የዝውውር ዋጋ ሲሆን፥ ከፍተኛ ሂሳብ ከወጣባቸው ታዳጊ ተጫዋቾች ደግሞ ቀዳሚው ተጫዋች አደርጎታል፡፡

በፒኤስጂ ቆይታው ከአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ በስተቀር ስድስት የሊጉ ዋንጫን ጨምሮ ሁሉንም አይነት በሀገሪቱ የሚዘጋጁ ዋንጫዎችን ማሳካት ችሏል፡፡

በ2020 ፒኤስጂን ለሻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ማብቃት የቻለ ቢሆንም ዋንጫውን ማሸነፍ ያልቻለው ምባፔ የክለቡ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው፡፡

ከብዙ የዝውውር ውዝግብ በኋላ በ2024 በነጻ ዝውውር የስፔኑን ታላቅ ክለብ ሪያል ማድሪድ ከተቀላቀለ በኋላ ከክለቡ ጋር የአውሮፓ ሱፐር ካፕን እንዲሁም የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫን አሸንፏል፡፡

ምባፔ ለሪያል ማድሪድ በፈረመበት የመጀመሪያ አመት በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ክብረወሰኑን የግሉ ከማድረጉም በተጨማሪ የአውሮፓ የወርቅ ጫማን አሸንፏል፡፡

በ2017 በ18 አመቱ ለፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን መጫወት የጀመረው ኪሊያን ምባፔ በ2018 የሩሲያ አለም ዋንጫ ሀገሩ ውድድሩን ስታሸነፍ በፍጻሜው ጨዋታ ግብ አስቆጥሯል፡፡

በዚህም በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ታሪክ በዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ግብ ያስቆጠረ በዕድሜ ትንሹ ተጫዋች ሲሆን፥ በዓለም ከፔሌ በመቀጠል 2ኛው ታዳጊ ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡

በውድድር ዓመቱ ባሳየው አስደናቂ ብቃት የዓለም ምርጡ ታዳጊ ተጫዋች ሽልማትን ያሸነፈው ኪሊያን የፈረንሳይ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ሽልማትን የግሉ አደርጓል፡፡

በተጨማሪም በ2021 ፈረንሳይ የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ዋንጫን እንድታሸንፍ ትልቁን ሚና የተጫወተ ሲሆን፥ በ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ ሀገሩ በፍጻሜው በአርንጀንቲና በመለያ ምት ተሸንፋ ዋንጫውን ስታጣ በጨዋታው ሦስት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

በውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የወርቅ ጫማን ያሸነፈው ኪሊያን በተከታታይ ሁለት የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታዎች ግብ በማስቆጠር ከብራዚላዊው ቫቫ ጋር ክብረወሰን ተጋርቷል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት 27ኛ አመት ልደቱን ያከበረው የሪያል ማድሪድ የግብ ማሽን በ2025 ብቻ ለክለቡ 59 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡

በዚህም በፖርቹጋላዊው የቀድሞ የሪያል ማድሪድ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ተይዞ የነበረውን በአንድ ዓመት ብዙ ግብ የማስቆጠር ክብረወሰን መጋራት ችሏል፡፡

በአጠቃላይ በእግር ኳስ ህይወቱ 411 ግቦችን በማስቆጠር ከካሪም ቤንዜማ (509) በመቀጠል 2ኛው በርካታ ግብ ማስቆጠር የቻለ ፈረንሳዊ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል፡፡

በ2023 በባሎንዶር ሽልማት 3ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው ኪሊያን ምባፔ በቀጣይ የሪያል ማድሪድ ታላላቅ ስኬቶች ፊት አውራሪ ሆኖ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.