የአማራ ክልል ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ÷ በክልሉ እየታየ ያለው ዘላቂ የሰላም ግንባታ ሒደት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
እንደ ሀገርም ሆነ በክልሉ እየተመዘገበ ያለው ሁለንተናዊ የልማት እመርታ የዜጎችን ተስፋ በእጅጉ ያሳደገና ተጠቃሚነታቸውን ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች በውጤታማነት እንዲፈጽም ም/ቤቱ በሕዝብ የተጣለበት ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በቅርቡ በክልሉ መንግሥትና ታጣቂ ኃይሎች መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት ለክልሉ ሕዝብ የሰላም ፍላጎት በእጅጉ ተስፋ ሰጪ መሆኑን አውስተዋል፡፡
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል።
በጉባዔው የተለያዩ አዋጆች እና ሹመቶች ለምክር ቤቱ አባላት ቀርበው እንደሚጸድቁ ይጠበቃል።
በደሳለኝ ቢራራ