ለ17ኛ ተከታታይ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ እየተሳተፈች የምትገኘው ቱኒዚያ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ለበርካታ ተከታታይ ዓመታት በመድረኩ በመሳተፍ ቀዳሚዋ ሀገር ናት ቱኒዚያ፡፡
በ35ኛው የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ በታሪኳ ለ21ኛ ጊዜ እየተሳተፈች የምትገኘው ቱኒዚያ ለ17ኛ ተከታታይ ጊዜ በአህጉሪቱ ትልቁ መድረክ ላይ ተገኝታለች፡፡
በፈረንጆቹ 1956 ነጻነቷን ከፈረንሳይ ያገኘችው ቱኒዚያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኗን በፈረንጆቹ 1957 መስርታለች፡፡
በዚሁ ዓመት ቱኒዚያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከአልጄሪያ ጋር አድርጋ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት መሸነፏ ይታወሳል፡፡
በፈረንጆቹ 1962 ቱኒዚያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈች ሲሆን ውድድሩንም ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ነበር ያጠናቀቀችው፡፡
በ1965 የአፍሪካ ዋንጫ መድረክን ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀችው ቱኒዚያ በወቅቱ ለፍጻሜ መድረስ ብትችልም በጋና ተሸንፋ ዋንጫውን ማጣቷ አይዘነጋም፡፡
ቱኒዚያ በታሪኳ አንድ ጊዜ ብቻ የአፍሪካ ዋንጫን ከፍ አድርጋለች፡፡
በፈረንጆቹ 2004 የአፍሪካ ዋንጫን ያዘጋጀችው ቱኒዚያ በፍጻሜው ሞሮኮን በማሸነፍ የዋንጫው ባለቤት መሆኗ ይታወሳል፡፡
በዚህም የአህጉሪቱን ትልቁን መድክ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅተው በሀገራቸው ካስቀሩ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዷ ሆናለች።
ቱኒዚያ ለተከታታይ 17 ዓመታት በመድረኩ በመሳተፍ ቀዳሚ ብትሆንም በአጠቃላይ ተሳትፎ ግን ግብፅ፣ ኮትዲቯር፣ ጋና እና ካሜሩን ይበልጧታል።
ግብፅ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር 27ኛ ተሳትፎዋን እያደረገች ሲሆን ኮትዲቫር 26፣ እንዲሁም ካሜሩን 22ኛ ተሳትፏቸውን እያደረጉ ነው፡፡
በሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ መሳተፍ ያልቻለቸው ጋና ደግሞ 24 ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር መሳተፍ ችላለች።
ቱኒዚያ በአጠቃላይ 21ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በማድረግ ብዙ ጊዜ በመድረኩ በመገኘትም አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ 3 ከናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ ጋር የተደለደለችው ቱኒዚያ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋን ከዩጋንዳ ጋር አድርጋ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ምድቡን እየመራች ነው።
በአሰልጣኝ ሳሚ ትራቤልሲ የምትመራው ቱኒዚያ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዋን የፊታችን ቅዳሜ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ከናይጄሪያ ጋር ታደርጋለች።
በአፍሪካ ዋንጫ 21ኛ ተሳትፎዋን እያደረገች የምትገኘው ቱኒዚያ በዓለም ዋንጫ መድረክ እስካሁን ስድስት ጊዜ ተሳትፎ አድርጋለች።
በ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ባደረገቻቸው 10 የምድብ ጨዋታዎች አንድም ግብ ሳይቆጠርባት ተጋጣሚዎቹ ላይ 22 ግቦችን በማስቆጠር 28 ነጥን በመሰብሰብ የምድቧ የበላይ በመሆን የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ማረጋገጧ ይታወሳል።
በዚህም አሜሪካ፣ካናዳ እና ሜክሲኮ በሚያዘጋጁት የ2026 የዓለም ዋንጫ ውድድር በታሪኳ 7ኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን የምታደርግ ይሆናል።
በወንድማገኝ ጸጋዬ